በላሊበላ በድምቀት የተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም ተጠናቋል--ፖሊስ

ላሊበላ (ኢዜአ) ታህሳስ 29/2015 በላሊበላ በድምቀት የተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም መጠናቀቁን ፖሊስ አስታውቋል።

አለም አቀፍ ቅርስ በሆነው ላሊበላ በድምቀት የተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ያለምንም ፀጥታ ችግር መጠናቀቁን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ፓሊስ ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ኮማንደር እንግዳው ሆዴነው ለኢዜአ እንደገለፁት በየአመቱ የሚከበረው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ ከተማ በደመቀ መልኩ ተከብሮ መዋሉን ተናግረዋል።

በበአሉም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የእምነት አባቶች፣ በሃገሪቱ ከአራቱም አቅጣጫዎች የመጡ እንግዶችን ጨምሮ የውጭ ሃገር ዜጎችና አምባሳደሮች በድምቀት አክብረውት መዋላቸውን ገልፀዋል።

በዓሉ በሰላም ለማክበር አስቀድሞ በተካሄደ የተቀናጀ የቅድመ ዝግጅ ስራ በዓሉን በሰላማዊ መንገድ ማክበር መቻሉን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፀጥታ ስራ መሰራቱን የገለፁት ኮማንደር እንግዳው፤ በዚህም የበዓሉን ታዳሚዎች ሰላም የሚነሳ ችግር አለመፈጠሩንም ተናግረዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበር ገልፀው፤ በተለይም 200 የሚደርሱ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ከፀጥታ ስራ ጎን ለጎን በዓሉን ለማክበር የመጡ እንግዶችን እግር በማጠብ ጭምር እገዛና ትብብር እንዳደረጉ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት እንግዶች በዓሉን አክብረው ወደ አካባቢያቸው እየተመለሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሩቅ ሃገር ለመጡ ደግሞ ማህበረሰቡ ባዘጋጀላቸው ግብዣ በዓሉን እያከበሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲውል አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ኮማንደሩ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም