በቦሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ የተከሰቱት የእሳት አደጋዎች ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጠር መቻሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በቦሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ የተከሰቱት የእሳት አደጋዎች ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጠር መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 29/2015 በቦሌ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ የተከሰቱት የእሳት አደጋዎች ከባድ ጉዳት ሳያደርሱ መቆጣጠር መቻሉ ተገለጸ።
በቦሌ ክፍለ ከተማ ቡልቡላ እየተባለ በሚጠራው አከባቢ ዛሬ ረፋድ ላይ በንግድ ቤቶች ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
አደጋው በክፍለ ከተማው ወረዳ 12 በሚገኙ ዘጠኝ የንግድ ቤቶች ላይ መከሰቱን የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጉልላት ጌታነህ ለኢዜአ ገልጸዋል።
አራት የሕንጻ መሳሪያ ቤቶች፣ ስጋት ቤት፣ ግሮሰሪ፣ ፈርኒቸር ቤት፣ የመኪና ዘይት መሸጫ፣ የልጆች ልብስ መሸጫ እና የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክተዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ 65 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማትረፍ መቻሉን ጠቁመዋል።
46 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች፣ 7 ከባድ እና 1 ቀላል ተሽከርካሪ እንዲሁም አንድ አምቡላንስ እሳቱን ለማጥፋት መሰማራታቸው ተገልጿል።
እሳቱን ለማጥፋት 1 ሰአት ከ35 ደቂቃ ፈጅቷል ያሉት አቶ ጉልላት 46 ሺህ ሊት ውሃ እና 500 ሊትር ፎም ጥቅም ላይ መዋሉን አመልክተዋል።
የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የገለጡት አቶ ጉልላት እሳቱን ለማጥፋት የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና ትናንት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ከአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ ከምሽቱ 5 ሰአት ከ12 ደቂቃ በመኖሪያ ቤት ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 500 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙም ተገልጿል።
መኖሪያ ቤቱ 200 ካሬ ሜትር የሚሸፍን እና የአራት አባውራዎች መኖሪያ መሆኑን አቶ ጉልላት ገልጸዋል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ማትረፍ መቻሉን በመግለጽ።
4 ሰዎች እና 1 የአደጋ ጊዜ ሰራተኛ በእሳት ቃጠሎው ቀላል የመቁሰል አደጋ እንዳጋጠማቸው ገልጸዋል።
61 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች፣ 10 ከባድ እና 1 ቀላል ተሽከርካሪ እንዲሁም 2 አምቡላንሶች እሳቱን ለማጥፋት ተሰማርተው እንደነበርም አስታውሰዋል።
የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ጉልላት ሕብረተሰቡ ኮሚሽኑ ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ሲያስተላልፋቸው የነበሩ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ሕይወቱንና ንብረቱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
ህብረተሰቡ አደጋዎች ሲያጋጥሙት በነጻ የስልክ መስመር 939፤ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011155 53 00 ወይም በ011156 86 01 በመደወል ማሳወቅ እንደሚችል አቶ ጉልላት ጠቁመዋል።