በቻን ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ዛሬ ምሽት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
በቻን ውድድር ላይ የሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ዛሬ ምሽት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደርጋል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 29/2015 ለአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር ዝግጅት ሞሮኮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ አቻው ጋር ዛሬ ምሽቱ 1 ሰዓት የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደርጋል።
በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ሰባተኛው የቻን እግር ኳስ ውድድር በአልጄሪያ አስተናጋጅነት ከጥር 5 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል።
በውድድሩ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ሞሮኮ በማቅናት ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ከጀመረ ዛሬ አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

ዋልያዎቹ ትናንት በካዛብላንካ በሚገኘው ላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ለሶስተኛ ቀን ልምምድ ሰርተዋል።
ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ በውድድሩ ላይ ከሚሳተፈው የሞሮኮ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ እንደሚያደርግ ኢዜአ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾቹ በመጀመሪያ ቀን የሞሮኮ ቆይታቸው ካደረጉት ረጅም ጉዞ አኳያ ቀለል ያለ ልምምድ መስራታቸውን ከፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ጋር በነበረው ቆይታ ገልጸዋል።

በነበረው ተከታታይ ልምምዶች የተሻለ ዝግጅት ማድረግ መቻሉም ነው የተመላከተው።
የሞሮኮው ዝግጅት አልጄሪያ ካለው የአየር ንብረት ጋር ለመላመድ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ብሔራዊ ቡድኑ ጥሩ የቡድን መንፈስ ላይ እንደሚገኝም ነው አሰልጣኝ ውበቱ የገለጹት።

የሞሮኮ ዋናም ሆነ የቻን ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ከሚገኙ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ጠንካራ የሚባል ስብስብ በመሆኑ የአቋም መለኪያ ጨዋታው ከአልጄሪያው ውድድር በፊት የተጫዋቾቹን ብቃት ለማየት የሚያስችል እንደሆነም ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር በምድብ አንድ ከአዘጋጇ አልጄሪያ እንዲሁም ሞዛምቢክ እና ሊቢያ ጋር ተደልድሏል።