ብዙ ኃላፊነቶችን ለሚሸከሙ ሴቶች ክብርና ፍቅር ይገባቸዋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

69
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 'ቤተሰብ ተሸክመው ለሚያሻግሩ ሴቶች የሚገባቸውን ክብር ሰጥተን መያዝ ካልቻልን ኢትዮጵያ አልገባችንም ማለት ነው' ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ተናገሩ። ዶክተር አብይ በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀ ''በማይንድ ሴት ኮንሰልት የአዳዲስ አስተሳሰቦችና የልሕቀት ግንባታ መድረክ'' ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። በመምሕርነት፣ በአመራርና በቤተሰብ ውስጥ ለሚገኙትና ግዙፍ የማሕበረሰብ አካል ለሆኑት ሴቶች ክብርና ፍቅር እንደሚገባቸውም ገልጸዋል። "የኢትዮጵያ ሴት ያልተሸከመችው ጉድ የለም" ሲሉ የተናገሩት ዶክተር አብይ 'ሴቶች በሆድ ውስጥ ጽንስ ይሸከማሉ፣ በጀርባቸው ሕጻን ያዝላሉ፣ በትከሻቸው ሰነፍ ባሎቻቸውን ያዝላሉ" ሲሉ የሚደርስባቸውን ማሕበረሰባዊ ጫና ገልጸዋል። "ኢትዮጵያ አንተ ነህ፣ ኢትዮጵያ አንቺ ነሽ ካልን፣ ኢትዮጵያን ተሸክሞ የሚሄደውን ማክበር ግዴታ ነው'' ያሉት  ዶክተር አብይ ሴቶች ክብር እንደሚገባቸው ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሴቶች በአገራቸው፣ በሰፈራቸው፣ በቤተሰባቸውና በስራቸው የሚያገኙት ክብርና እኩልነት የአገሪቱ ዋነኛ የስልጣኔ መገለጫ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። ሴትን የሚንቅና የሚያንገላታ ሕዝብ ያልሰለጠነ ብቻ ሳይሆን መቼም የማይሰለጥን እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አብይ ወንዶች ከዛሬ ጀምሮ በሚሄዱበት ስፍራ ሁሉ ሴቶችን በማክበር ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም