የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮች የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ጎበኙ

ላሊበላ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 የተለያዩ ሀገሮች አምባሳደሮች የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን ዛሬ ጎበኙ።

የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናትን የጎበኙት ከአስር ሀገራት በላይ አምባሳደሮች ናቸው።

የቱሪዝም ፍሰቱ በኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እና አጋጥሞ በነበረው ጦርነት ሳቢያ ተቀዛቅዞ እንደነበር የቱሪዝም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በዚሁ ጊዜ አስታውሰዋል። 

የአምባሳደሮቹ ጉብኝት ይህን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና ጦርነት ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የቱሪዝም ዘርፉ መልሶ እንዲነቃቃ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ራሱን የቻለ አበርክቶ እንደሚኖረውም ሚኒስትር ዴታው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም