አቶ ኢሳያስ ጅራ የሴካፋ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ተመረጡ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል።

የሴካፋ የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ በዛንዚባር የአባል አገራት እግር ኳስ ፌዴሬሽን አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ተካሄዷል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በድጋሚ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት የሴካፋ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ መመረጣቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

አቶ ኢሳያስ ከእ.አ.አ 2018 አንስቶ ሴካፋን በምክትል ፕሬዝዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ።

በጉባኤው ላይ በተደረገው ሌላኛው ምርጫ የታንዛንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዋላስ ካሪያ በድጋሚ በፕሬዝዳንትነት መመረጣቸውን ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም