በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲፈለግ የነበረው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል ሲፈለግ የነበረው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውሎ በፍርድ ሂደት ላይ እያለ የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ አምልጦ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው ኪዳነ ዘካርያስ ሱዳን ውስጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
በስደተኞች ላይ በሚፈጽመው የጭካኔ ተግባርና ግፍ የተሞላበት አያያዝ የሚታወቀው አደገኛ የሰዎች አዘዋዋሪ ኪዳነ ዘካርያስ ሀብተማርያም የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት (INTERPOL) በኩል በአሰራጨው መረጃ መሠረት በሱዳን በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ተጠርጣሪው በምስራቅ አፍሪካ ስደተኞች ላይ ከሚደረገው አፈና፣ ዝርፊያ እና ግድያ ጀርባ ያለውን ትልቅ የወንጀለኛ ድርጅትን በመምራት በኢትዮጵያ እና በኔዘርላንድስ ስደተኞችን በህገ-ወጥ መንገድ በማዘዋወርና በሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ በሁለት የኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያዎች ይፈለግ እንደነበር ይታወቃል።

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት፣ የዓለም አቀፍ የፖሊስ ኅብረት ድርጅት (INTERPOL)፣ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ የኔዘርላንድስ ፖሊስ፣ ኢሮፖል እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች በጋራ በመተባበር ባቋቋሙት ግብረ-ሃይል መካከል በተደረገው የመረጃ ልውውጥ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት ፕሬዚዳንት ግብረ-ኃይሉ ሌት ተቀን በአደረጉት ብርቱ ክትትል በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለግ የነበረው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ ሊያመልጥ እንደማይችል ማሳያ እንደሆነ ተናግረው የተጠርጣሪው መያዝ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ገልፀዋል።
ከምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ኅብረት ድርጅት እና ከኢንተርፖል አባል ሀገራት ጋር በመተባበር በተጠርጣሪው ዙሪያ እያካሄዷቸው ያሉ ተጨማሪ ምርመራዎች የቀጠሉ ሲሆን በዚህም ሌሎች በዓለም አቀፍ ደረጀ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋውን የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ለመበጣጠስ ለጀመረው የተጠናከረ ኦፕሬሽን ኅብረተሰቡ ከፖሊስ ጎን ሆኖ የተለመደውን ቀና ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።