ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው-ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ - ኢዜአ አማርኛ
ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው-ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ታህሳስ 28/2015 በሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚያደርጉት ሂደት የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ አስታወቁ።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት አራት ቀናት “በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ተጠናቋል።

መድረኩን የመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ የውይይቱን አላማ መሰረት በማድረግ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ አኩሪ ታሪክ ያላት ታላቅ ሀገር ናት።
ይሁንና የሀገር ግንባታ ስራው ባለመጠናቀቁ በየጊዜው የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሟት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብዝሃ ህዝብ ያላት ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትሩ "ከዚህ በሚጻረር መልኩ ጽንፈኝነትና ብሔርተኝነት የጋራ እሴቶቻችንን በመሸርሸር አንድነታችንን እየጎዱት ይገኛሉ" ብለዋል።
በሀገር ግንባታ ረገድ ምሁራን በሚፈለገው ልክ ተሳታፊ አለመሆናቸው የችግሩ አንድ መንስኤ እንደሆነም አመልክተዋል።

መንግስትና ምሁራን ለሀገር እድገት ተቀራርቦ መስራት እንዲችሉ ታሳቢ በማድረግ የምሁራን የውይይት መድረክ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ ምላሽ ያላገኙ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ኢትዮጰያውያን ችግሮቻችንን ብሔራዊ ጥቅማችንን ባስከበረ መልኩ ለመፍታትና ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል የተቋቋመው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ዓላማ እንዲሳካ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት በሚሰራው ስራ ምሁራን ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

ከመድርኩ ተሳታፊዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር አቤኔዘር ሉቃስ በበኩላቸው የበለጸጉ ሀገራት ያጋጠማቸውን ችግሮች የፈቱትና የተሻገሩት በምሁራን ተሳትፎ መሆኑን ተናግረዋል።
"በመሆኑም ምሁራን ለሀገር ዕድገትና ብልጽግና ሚናችንን ማጎልበት አለብን " ብለዋል ።"
መንግስት ሀገር አቀፋዊ ሰነድ በማዘጋጀት ምሁራንን ማወያየቱ በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ እንድንሆንና ከመንግስት ጋር ተቀራርበን እንድንሰራ ያግዘናል" ሲሉም አክለዋል።
"ለሀገሬ የሚጠበቅብኝን በሙሉ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ "ያሉት መምህሩ በተለይም ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለያዛቸው ዕቅዶች መሳካት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አመልከተዋል።

"በሀገራችን ለሚቀረጹ ፖሊሲዎችም ሆነ በሀገርና በተቋም ግንባታ ምሁራን የላቀ አስተዋጽኦ እንድናበረክት ከውይይቱ ጠቃሚ ግብዓት አግኝተናል" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ታሪኳ ወልደመድህን ናቸው።
በተለይም የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማወያየት መፍትሄ ለማምጣት እየሠራ መሆኑን ያመለከቱት ምክትል ፕሬዝዳንቷ የኮሚሽኑ ዓላማ እንዲሳካ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።