ባህላዊ ስፖርቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በትምህርት ቤቶች ስልጠና እየተሰጠ ነው- የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2015 (ኢዜአ) ባህላዊ ስፖርቶች ለዘመናዊ ስፖርቶች መነሻ እንደመሆናቸው ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በትምህርት ቤቶች የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶችን በመክፈት ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

14ኛው የአዲስ አበባ ከተማ የባህል ስፖርቶች ፌስቲቫልና ውድድር በጃን ሜዳ ስፖርት ትምህርትና ሥልጠና ማዕከል ዛሬ ተጀምሯል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዳዊት ትርፉ በመርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የባህል ስፖርቶችን ማሳደግ፣ ማስፋፋትና ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲኖራቸው መሥራት ይገባል።

ከስፖርት እንቅስቃሴ ጠቀሜታው ባሻገር መጪው ትውልድ ባህሉን፣ ትውፊቱንና ማንነቱን እያወቀ እንዲሄድ ያደርጋል ሲሉም አመልክተው የባህል ስፖርቶች ለዘመናዊው ስፖርት መነሻ እንደመሆናቸው የተለየ ትኩረት በመስጠት መሥራት እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ቢሮው የባህል ስፖርቶችን ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑንና አሁን ላይ የባህል ስፖርት በትምህርት ቤቶች የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶችን በመክፈት ሥልጠና እየሰጠ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ እንደ አገር ካሉን በርካታ የባህል ኃብቶች አንጻር የባህል ስፖርቶችን ተጠብቀውና በመጤ ባህሎች ሳይበረዙ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ነው የገለጹት።

በተለይ መገናኛ ብዙኃን በዚህ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

ዛሬ የተጀመረው 14ኛው ከተማ አቀፍ የባህል ስፖርቶች ውድድርና ፌስቲቫል በዘጠኝ የባህል ስፖርት ዓይነቶች የሚደረግ ሲሆን፤ ውድድርና ፌስቲቫሉ እስከ ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቀጥል ይሆናል።

በዛሬው የመክፈቻ መርሃ-ግብር  በስፖርት ጋዜጠኞችና በአርቲስቶች መካከል የገና ጨዋታ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፣ የስፖርት ጋዜጠኞች 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

እንዲሁም በወንዶች በተካሄደው የፈረስ ሸርጥ ውድድር የካ ክፍለ ከተማ አንደኛ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ ሲወጣ፤ ቦሌ ክፍለ ከተማ ደግሞ የሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

በሴቶች የፈረስ ሸርጥ ውድድር ደግሞ የካ ክፍለ ከተማ አንደኛ፣ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ሁለተኛ እና  ቦሌ ክፍለ ከተማ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም