ምሁራን በሀገር ግንባታ ላይ ያልተገደበ ሚናቸውን በመወጣት አበርክቷቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ ተገለጸ

ዲላ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2015 (ኢዜአ) ምሁራን በሀገር ግንባታ ላይ ያልተገደበ ሚናቸውን በመወጣት አበርክቷቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ አስገነዘቡ።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ "በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የሀገር ግንባታ ሥርዓታችንን ከፍ ለማድረግ የምሁራን ሚና ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው ብለዋል።

የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመረውን የለውጥና የሀገር ግንባታ ጉዞ ለማስቀጠል ምሁራን የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።

በተለይ ሀገርና ህዝብ ችግር ውስጥ ሲገባ ምሁራን በገለልተኝነት የመፍትሄ አቅጣጫ የማመላከት ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች ያልተገደበ ሚናቸውን በመወጣት ለሀገር ግንባታ አበርክቷቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በውይይቱ ለሀገር ግንባታ ገንቢ ሀሳቦችና ሌሎች ጉዳዮች ተነስተው ሰፊ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

እንደ ሀገር ከድህነት አዙሪት ውስጥ ለመላቀቅ የጋራ ጥረት እንደሚጠይቅ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ በዚህ ረገድ ምሁራን ከመጠየቅ ባለፈ ግንባር ቀደም ሚናቸውን በተገቢው መወጣት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ  በበኩላቸው ምሁራን በሀገር ግንባታ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ መድረኩ እንዲመቻች መደረጉ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም  ምሁራን ለፖሊሲና ለሀገር ግንባታ ገንቢ ሃሳብ በማዋጣት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይ የፖለቲካ ስርዓታችንን ከመጠፋፋት ወደ መገነባባት ባህል እንዲሸጋገር ምሁራን በቁርጠኝነት መስራት አለብን ብለዋል።

ሀገር የጋራ በመሆኗ ሁላችንም በየደረጃው በስራ ድርሻችን ልንግባባ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ ዶክተር አዲስዓለም ብርሃኑ ናቸው።

መድረኩ በሀገር ግንባታ ሚናችንን ለይተን የድርሻችንን ለመወጣት የሚያስችል ነው በማለት ገልጸው፤ ምሁራን የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ማመንጨት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በመድረኩ መምህራን፣ ቴክኒካል ረዳቶችና የአስተዳደር ዘርፍ አመራሮች ለውይይት በቀረበው ሰነድና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ  በስፋት በመወያየት መድረኩን አጠናቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም