በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ሙያዊ እገዛ ለማድረግ የተቋቋመው "ኢትዮጵያ 2050 ኢኒሼቲቭ" የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

115

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 26/2015 በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ሙያዊ እገዛ ለማድረግ የተቋቋመው "ኢትዮጵያ 2050 ኢኒሼቲቭ" የመምህራንን አቅም ለማጎልበት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ የትምህርት ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

"ኢትዮጵያ 2050 ኢኒሼቲቭ" በውጭ እና በአገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንን በጋራ ያሰባሰበ ኢኒሼቲቭ ነው፡፡

ኢኒሼቲቩ በዋናነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2050 ይደርሳል ተብሎ የሚገመተውን አሃዝ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተለያዩ መስኮች ሙያዊ እገዛ እንደሚያደርግም ነው የተጠቆመው፡፡

በዚህም በትምህርት፣ በውኃና ኢነርጂ አቅርቦትና ኢንዱስትሪ ልማትን ጨምሮ በሌሎች መሰረታዊ ዘርፎች ሙያዊ እገዛ  እንዲሁም ጥናታዊ ምክረ-ሀሳቦችን ያቀርባል፡፡   

ኢኒሼቲቩ ሥራውን ለማሳለጥ የትምህርት፣ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ/ሰው ሰራሽ አስተውሎት/፣ውሃና ኢነርጂ እና ማኑፋክቸሪንግ ላይ ትኩረት ያደረገ  አምስት ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።

በዛሬው እለትም የኢኒሼቲቩ አባላት የሆኑ የዩኒቨርሲቲ መምህራን "በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ምን ላይ እናተኩር? " በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት አካሂደዋል፡፡  

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ዘመናዊ የትምህርት ታሪክ፣ መጀመሪያ፣ ሁለተኛ እና ከፍተኛ ትምህርት ያሉበት ደረጃ እና ችግሮች እንዲሁም መፍትሔዎች ላይ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ምክክር ተደርጎበታል።    

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደ 26 ነጥብ 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ተማሪዎችን በሚፈለገው ልክ በእውቀትና ክህሎት በማብቃት የአገር እድገት መሰረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፤ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ የመምህራን የእውቀትና ክህሎት አቅም ሲጎለብት ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ኢኒሼቲቩ መምህራንን በማሰልጠንና አቅማቸውን በመገንባት ረገድ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ትምህርት እና ምርምር ላይ ትኩረት ያደረጉ የልህቀት ማዕከላትን ማጠናከር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ መሰረት በመሆኑ ኢኒሼቲቩ በዚህም ላይ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።  

"ኢትዮጵያ 2050 ኢኒሼቲቭ" የትምህርት ግብረ-ኃይል መሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በበኩላቸው፤ ግብረ- ኃይሉ በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት እንዲመጣ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የዛሬው የውይይት መድረከም የዚሁ አካል መሆኑን ነው ያብራሩት፡፡   

ከታችኛው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ የተናበበ የትምህርት ሥርዓት መኖር ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

በኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማትና የተማሪዎች ቁጥር በመጨመር ረገድ ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ደግሞ  የወላይታ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የግብረ-ኃይሉ አባል ወይዘሮ ኤላዛር ታደሰ ናቸው፡፡

ነገር ግን የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡   

በመሆኑም የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት የሚከናወኑ ሥራዎች ጥራት ከማስጠበቅ ጋር ተጣጥመው ሊከናወኑ እንደሚገባ ተናግረዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም