መንግስት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ ነው

አርባምንጭ/መቱ ታህሳስ 26/2015 (ኢዜአ) መንግስት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ምሁራን ለሀገር ግንባታ የሚውሉ ሐሳቦችን ለማንሸራሸርና የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርቧል።

የመቱ ዩኒቨርሲቲ እና የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን "ለሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ እየተወያዩ ነው።

በመቱ ዩኒቨርሲቲም የዩኒቨርሲቲውን ምሁራን ያሳተፈ መድረክ ዋናው ግቢ እየተካሄደ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የዩኒቨርሲቲዉ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ እንዳሉት ምሁራን ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊና ፈጣን ዕድገት እንዲሁም ለሕብረተሰብ ለውጥ መትጋት አለባቸው።

የኢትዮጵያ ምሁራን ጠንካራ እና ሀገር አሻጋሪ አቋም ይዘው በአስተሳሰቦች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ፣ ዕውቀትን መሰረት አድርገው ኢትዮጵያን በልማት እና እድገት ለማራመድ የተጀመረውን ጉዞ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በዕውቀት እና በክህሎት እንዲሁም በመልካም ስነ ምግባር የታነጹ ሀገር ወዳድና ችግር ፈቺ ትውልድን የማፍራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

መንግስት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ቁርጠኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ምሁራን ለሀገር ግንባታ የሚውሉ ሃሳቦችን ማንሸራሸር ይገባቸዋል ብለዋል።

የመቱ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር እንደገና አበበ ዩኒቨርሲቲው የሀገር ሁለንተናዊ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ውይይት እየተካሄደ ነው።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትርና የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እንዳሉት ምሁራን ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ ጥናቶችና ምርምሮች በማካሄድ ለአገር የልማትና እድገት ሚናቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል።

ኢትዮጵያን ለመገንባት የምሁራን ድርሻ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በመሆኑም በብሔራዊ አጀንዳዎች የጋራ መግባባት በመፍጠር የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች በዕውቀትና እውነት ላይ በመመስረት ለችግሮች መፍትሄ ከማበጀትም በላይ ዜጋውንና ሀገሩን የሚወድ ግብረ ገብ ትውልድ በመፍጠሩ ረገድ በባለቤትነት ልሠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ እንዳሉት ሁሉም ሰው በአገር ግንባታ ውስጥ የራሱ ሚና ቢኖረውም ምሁራን በሀገርና ትውልድ ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለባቸው ናቸው።

በዚሁ መነሻነት በእውነትና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ጥናትና ምርምር በማድረግና የሀሳብና የሞራል ግንባታ ላይ ግንባር ቀደም ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በተለይም ለሀገር ዕድገትና ልማት መፋጠን አቅም የሚሆኑ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማድረግ ለመንግስት ፖሊሲ ግብአት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ውይይት መክፈቻ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋና፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊና ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም