የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማእድንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአቱ ለማስገባት እየሰራ መሆኑን ገለጸ

ጎንደር /ኢዜአ/  ታህሳስ 26/2015 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማእድንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአቱ ለማስገባት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ምርት ገበያው በቅርቡ ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአቱ የሚያስገባቸውን ስንዴን ጨምሮ አራት የግብርና ምርቶችን ለአጋር አካላት የሚያስተዋወቅ የውይይት መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ አካሂዷል፡፡

የምርት ገበያው የህግ ማስከበሪያ ዋና ኦፊሰር አቶ ሽመልስ ሀብተማርያም እንዳሉት ምርት ገበያው ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ የማእድንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማገበያየት የሚያስችለው ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡

ምርት ገበያው ባገኘው ፈቃድ መሰረት የኢንዱስትሪና የማእድን ምርቶችን በማጥናት ወደ ግብይት ስርአቱ ለማስገባት የሚያስችለውን ሂደት እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአቱ የሚገቡ የማእድን አይነቶችም ሳፋየር፣ ኢመራልድና ኦፓል የተባሉት ሲሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶች ደግሞ ሲሚንቶን የመሳሰሉ ምርቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡  

የማእድን ምርቶችን በተመለከተም ከማእድን ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነዶች መፈረማቸውንና ከሁለቱ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች ስምምነቱ ሊኖረው ስለሚገባው ይዘት ጥናት በማድረግ ረቂቅ ውል የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪና የማእድን ምርቶቹ ወደ ዘመናዊ የግብይት ስርአቱ እንዲገቡ መታቀዱ በምርቶቹ ላይ የሚፈጸመውን ህገ-ወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ በማስቀረት ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል፡፡

ምርት ገበያው በዚህ አመት የሀገራችን ግብርና ምርቶች የሆኑትን ስንዴን ጨምሮ ሩዝ፣ ግብጦ፣ ባቄላና ኮረሪማ ወደ ዘመናዊ ግብይት ስርአቱ እንደሚያስገባም አብራርተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት በጎንደር 'ሪጂናል የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማእከል' ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ የግብርና ምርቶች ግብይት መፈጸሙን የገለጹት ደግሞ የማእከሉ ሃላፊ አቶ ባየልኝ ዘርአይ ናቸው፡፡

ማእከሉ ካገበያያቸው የግብርና ምርቶች መካከልም ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ማሾ በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለማእከላዊ፣ ሰሜን፣ ደቡብና ምእራብ ጎንደር ዞኖች የ'ኤሌክትሮኒክስ ግብይት' አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሰብልና የኢንዱስትሪ ምርቶች ዳይሬክተር አቶ ልንገረው ሀበሻ በበኩላቸው የሚስተዋሉ ችግሮችን ምርት ገበያው ፈጥኖ እንዲያስተካክል ጠቁመዋል፡፡  

ምርት ገበያው ባለፉት 14 አመታት 308 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ከ7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የግብርና ምርቶችን በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ባቋቋማቸው 6 የኤሌክትሮኒክስ የግብይት ማእከላት በኩል ማገበያየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በውይይት መድረኩ ከሰሜን፣ ደቡብና ማእከላዊ ጎንደር ዞኖች የተውጣጡ ከገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየኖች ከግብርናና ከንግድ መምሪያዎችና ክልል ቢሮዎች የተውጣጡ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም