ተፋሰሶችን ከደለል ለመከላከል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት የማልማት ስራ መከናወኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ

162

ሃዋሳ(ኢዜአ)  ታህሳስ 26 ቀን 2015  ተፋሰሶችን ከደለል ለመከላከል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የማልማትና የእንክብካቤ ስራ መከናወኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴሩ የስምጥ ሸለቆ ቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስር ባሉ ተፋሰሶች በተከናወኑ  ስራዎች ላይ  በሻሸመኔ ከተማ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ፤ ከተከናወኑት ስራዎች መካከል በስምጥ ሸለቆ ቤዚን ስር ባሉ አባያና ጫሞ፣ሃዋሳና ዝዋይ ሻላ ንኡስ ተፋሰሶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ስራዎቹ የተከናወኑት ባለፉት አምስት ዓመታት እንደሆነ ገልጸው፤ በዚህም ውጤት እየመጣ መሆኑን በየአካባቢው ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች በተሰራው ጥናት ማረጋገጥ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በስራውም ወደ ሃይቆቹ የሚገባውን የደለል ክምችትና የጎርፍ አደጋ መቀነሱን እንዲሁም  የተፋሰሱን ዙሪያ በማልማትም ህብረተሰቡ በተለያየ ስራ ተሰማርቶ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተፋሰሱ አካባቢ ባሉ ወረዳዎች የተከናወኑ ስራዎችን  ማህበረሰቡ እንዲያስቀጥለው በማድረግ ተሞክሮውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፋት ስራ በቀጣይ እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡

እንደ ሃገር ሃይቆቹ በደለል እንዳይሞሉ ከመከላከል በተጨማሪ የሃይቆቹን ደህንነት በመጠበቅ የተለያዩ የልማት ስራዎች ማከናወን፣ ኢንደስትሪዎች ያሉባቸውን ተፋሰሶች ከብክለት ነጻ የማድረግና ጥራቱን የመጠበቅ ስራም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የስምጥ ሸለቆ ቤዚን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዴቢሶ ዴዴ፤ በአባያና ጫሞ፣ሃዋሳና ዝዋይ ሻላ ንኡስ ተፋሰሶች ስር ባሉ 24 በሚደርሱ ወረዳዎች የልማትና እንክብካቤ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የአፈርና ውሃ ጥበቃ፣ሃይቆቹን ከደለል የመከላከል፣የአረንጓዴ ልማትና ተፈጥሮን ሊጎዱ በሚችሉ ስራዎች የተሰማሩ ሰዎች  በለሙ መሬቶች ላይ በተለያየ ዘርፍ የማሰማራት ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት የተጀመሩ ስራዎችን የማጠናቀቅና በሃዋሳ ሃይቅ ዙሪያ ጨለለቃ ተፋሰስ ላይ የአረንጓዴ ልማት ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል፡፡

በተፋሰሱ ዙሪያ በተከናወነው የልማትና እንክብካቤ ስራ ከ500 ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን የገለጹት ደግሞ በመድረኩ የተሳተፉ በሃዋሳ ከተማ አስተዳደር የሃዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ዘርፍ ሃላፊው አቶ ለማ ኪዳኔ ናቸው፡፡

በዚህም በንብ ማነብና ዶሮ እርባታ የተሰማሩና በችግኝ ጣቢያው የስራ እድል የተፈጠረላቸው ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ማድረጉንና የተጀመሩ ስራዎች ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ በተፋሰሶቹ በተከናወኑ ስራዎች የመጣው ውጤት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተሰራው ጥናት ተደግፎ የቀረበ ሲሆን በቀጣይ በሚተኩርበት  ስራዎች ላይ ውይይት ተካሄዷል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም