ህብረተሰቡ የገና በዓልን ሲያከብር ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ነገሮች እንዲጠነቀቅ ኮሚሽኑ አሳሰበ

183

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ታህሳስ 26/2015 የገና በአል ሲከበር ህብረተሰቡ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ነገሮች እንዲጠነቀቅ የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል ተጠቃሽ የሆነው የገና በዓል የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን ይከበራል።

በመሆኑም በዓሉ ሲከበር በተለይም ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳስቧል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጉልላት ጌታነህ፤ በዓሉ ሲከበር ለአደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ የተለያዩ ነገሮች ስላሉ ጥንቃቄ ያሻቸዋል ብለዋል።

ለስራ ፍጥነት ሲባል በአንድ የኤሌክትሪክ ማከፋፋያ ላይ የተለያዩ አገልግሎቶችን መጠቀም ለአደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

በምግብ ማብሰልና ሌሎችም አገልግሎቶች ወቅት ከአካባቢው ተቀጣጣይ ነገሮችን ማራቅና ሻማና ሌሎችንም ነገሮች ለኩሶ መሄድም የአደጋ መንስኤ ሊሆን ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በመሆኑም የገና በአል ሲከበር ህብረተሰቡ ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ አጋላጭ ነገሮች እንዲጠነቀቅ አቶ ጉልላት አሳስበዋል።

በበዓሉ ወቅት ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥም በፍጥነት ለመቆጣጠር ከተለያዩ ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በውሃ አቅርቦቱ ከውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን እንዲሁም ከኤሌክትሪክ ጋር ያለውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር በመተባበር ለአደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

እሳትና ድንገተኛ አደጋ ቢያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ 011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ ይቻላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም