በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር አላማውን እንዲያሳካ ምሁራን አስታራቂ እሴቶችን አጉልተው በማውጣት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር አላማውን እንዲያሳካ ምሁራን አስታራቂ እሴቶችን አጉልተው በማውጣት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

ጂንካ፣ ታህሳስ 25 ቀን 2015 (ኢዜአ) ምሁራን በአገሪቱ የሚገኙ ብዝሃ ባህሎች ውስጥ ያሉ ጠቃሚና አስታራቂ እሴቶችን በጥናትና ምርምር አጉልተው በማውጣት ለአገራዊ ምክክር መድረኩ እንዲውሉ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
''በአገር ግንባታ የምሁራን ሚና''በሚል መሪ ሀሳብ በጂንካ ዩኒቨርስቲ ሲካሄድ የነበረው የምሁራን የምክክር መድረክ ተጠናቋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል አስተባባሪ ዛዲግ አብርሃ፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ እና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በምክክር መድረኩ ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቅርቡ ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ የምክክር መድረክ አላማውን አሳክቶ በስኬት እንዲጠናቀቅ ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በትምህርት ቤቶች፣ በኮሌጆች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተወያይተው ችግሮችን መፍታት የሚችሉበት ልምድ መጎልበት እንዳለበት ገልጸው፤ በተለይ ምሁራን ለዚህ ላቅ ያለ ድርሻ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ምሁራን በሚሰሯቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች በአገሪቱ በሚገኙ ብዝሃ ባህሎች ውስጥ ያሉ ጠቃሚና አስታራቂ እሴቶች አጉልቶ በማውጣት ለምክክር መድረኩ እንዲውሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ምሁራን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፤ በትክክለኛና በተጨባጭ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ ህዝቡን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ መምራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በእውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ በመያዝ መሞገትና ማሳመን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባል የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ፤ ከምሁራን ጋር እየተደረገ ያለው ምክክር በቀጣይ ሊደረግ የታሰበው አገራዊ የምክክር መድረክ ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
ከሚያግባቡን አያሌ ጉዳዮች ይልቅ በሚያለያዩን ጥቂት ነገሮች ስናተኩር ከርመናል ያሉት አቶ ንጋቱ፤ በአገራዊ ምክክር መድረኩ መግባባት ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል።
ጠንካራ አገረ መንግስት ለመገንባት ህዝቡን ወደ አንድ አገራዊ አስተሳሰብ ማምጣት እንደሚገባ ጠቁመው፤ በዚህም ምሁራን የሚያግባቡ እና አስታራቂ ሀሳቦችን በማመንጨት ብሄራዊ የምክክር መድረኩ ፍሬያማ እንዲሆን መስራት አለባቸው ብለዋል።
ሀገር ለመገንባት ጠንካራ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል ያሉት አቶ ንጋቱ በተቋም ግንባታም ምሁራን የነቃ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስረድተዋል።