ለሰላም ስምምነቱ ይበልጥ ውጤታማነት ምሁራን ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል---አቶ ጥራቱ በየነ - ኢዜአ አማርኛ
ለሰላም ስምምነቱ ይበልጥ ውጤታማነት ምሁራን ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል---አቶ ጥራቱ በየነ

ጎንደር (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015---"የሰላም ስምምነቱ ይበልጥ ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን ምሁራን በእውቀት ላይ የተመሰረተ አስተዋጾ ማበርከት አለባቸው'' ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ ተናገሩ፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ለኢዜአ እንደገለጹት በመላ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አዲስ ተስፋ የፈነጠቀው የሰላም ስምምነት ዘላቂ በሆነ መንገድ ማስቀጠል እንዲቻል የምሁራን ድርሻ የላቀ ነው።
ጦርነቱ እንደ ሀገር ካስከፈለው ዋጋ ባለፈ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የፈጠረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በበሰለ አመራር ሰጭነት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
"የሰላም ስምምነቱ ጦርነቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቋጭ በር የከፈተ ታሪካዊ እርምጃ ነው" ያሉት አቶ ጥራቱ፣ ስምምነቱ የበለጠ ውጤታማና ዘላቂ እንዲሆን ምሁራን በእውቀት ላይ የተመሰረተ አጋርነታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
"የተጎዳው ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያገግም አዳዲስ የፖሊሲ ሀሳቦችን በማመንጨት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል።
ከሰላም ስምምነቱ በተቃራኒ የቆሙ አካላትን በሃሳብ የበላይነት በመመከት በኩልም የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አቶ ጥራቱ አመልክተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ምሁራን አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ተገንዝበው ህዝቡን በማንቃት፣ በማወያየትና ሰላምን በመገንባት ሂደት የጎላ ሚና ሊጫወቱ ይገባል።
ሀገር ከገጠማት ችግር እንድትወጣ በማድረግ በኩል የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ናቸው።
የሰላም ስምምነቱ እንደ ሀገር አስፈላጊና ጠቀሜታውም የላቀ መሆኑን ጠቁመው፣ "በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ሂደት ምሁራን በተደራጀ አግባብ የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው ይቀጥላሉ" ብለዋል።
መንግስት የጀመረውን የሰላም ጥረት ያደነቁት ዶክተር አስራት፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለሰላም ስምምነቱ መሳካት በእውቀትና በፖሊሲ ሃሳቦች እገዛውን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
"የምሁራን ሚና በሀገር ግንባታ'' በሚል መሪ ሃሳብ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በትናንትናው እለት ውይይት መጀመራቸው መገለጹ የሚታወስ ነው።