በአማራ ክልል ለተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ውጤታማነት አመራሩ ሚናውን ሊወጣ ይገባል--ዶክተር ይልቃል ከፋለ

ባህር ዳር(ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 -በአማራ ክልል በበጋ ወራት ለሚካሄደው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ውጤታማነት አመራሩ ግንባር ቀደም ሆኖ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አሳሰቡ።

በክልሉ በበጋ ወራት ከ310 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

በዘንድሮ የበጋ ወራት ክልላዊ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ይልቃል በመድረኩ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ዘንድሮ የሚከናወነው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የተፈጥሮ ሚዛንን በሚጠብቅ መልኩ በጥራት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያለው አመራር የዘንድሮው የበጋ ወራት የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ በውጤታማነት እንዲከናወን ትኩረት ሰጥቶ ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው፣ "በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ310 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ነባር እና አዲስ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ይከናወናል" ብለዋል።

የልማት ሥራው በተለዩ 8 ሺህ 548 ተፋሰሶች ላይ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ከጥር ወር 2015 ዓ.ም መግቢያ ጀምሮ የሚከናወን ሲሆን ለሥራው የሚያግዙ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን የተለያዩ መሳሪያዎች እንዲዘጋጁ መደረጉንም ተናግረዋል።

በዚህ የልማት ሥራ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ህዝብ እንደሚሳተፍ የገለጹት ዶክተር ኃይለማርያም፣ "የልማት ሥራው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በአማካኝ ለ23 የሥራ ቀናት ይከናወናል" ብለዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራው ጥራቱን ጠብቆ እንዲሰራ በየደረጃው ተገቢ ሙያዊ እገዛ እንደሚደረግም አመልክተዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ አተኩሮ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም