የሀገሪቷ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

አዳማ (ኢዜአ) ታህሳስ 25/2015 የሀገሪቷ ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ምሁራን የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፎዚያ ካሳ ገለጹ።

''በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና'' በሚል መሪ ሃሳብ በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ፎዚያ ካሳ እንደገለፁት ምሁራን በሀገር ግንባታ ውስጥ ትልቅ ሚና አላቸው ብለዋል።

በተለይ የሀገር ልማትና ዕድገት ቀጣይነት የሚረጋገጠው የምሁራን ተሳትፎ ሲታከልበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ምሁራን የልማት ፕሮግራሞችን በጥናትና ምርምር በመደገፍ የሀገሪቷ ዕድገትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

በዚህም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ምሁራን ከፍተኛውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸውም ጨምረው ገልጸዋል።

የአርሲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዱጉማ አዱኛ በበኩላቸው የሀገሪቷ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በዘላቂነት የሚረጋገጠው የምሁራን ዕውቀት ሲታከልበት ነው ብለዋል።

''የሀገሪቷ ልማት በዕውቀት፣ በጥናትና በምርምር ለመደገፍ የሚናችንን መወጣት አለብን'' ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም