ብራዚላውያን ለእግር ኳስ ኮከብ ፔሌ የመጨረሻውን ስንብት እያደረጉ ነው

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 24/2015 ብራዚላውያን የእግር ኳሱ ኮከብ ለነበረው ፔሌ የመጨረሻ ሽኝት እያደረጉ ነው።

የብራዚል መንግስት በፔሌ ሕልፈት ምክንያት ለሶስት ቀናት ያወጀችው ብሔራዊ ሃዘን ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

ፔሌ በታዳጊነቱ እግር ኳስ በጀመረበት በብራዚሉ ሳንቶስ ክለብ ኡርባኖ ካልዴይራ ስታዲየም ከዛሬ ማለዳ አንስቶ ተጫዋቹን የሚዘክሩ ዝግጅቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።

ብራዚላውያን የፔሌ አስክሬን ለሽኝት ባረፈበት ስታዲየም በመገኘት የመጨረሻ ስንብት እያደረጉ መሆኑን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

መርሐግብሩ ዛሬ ሳይቋረጥ ለ24 ሰአት እንደሚከናወን ተነግሯል።

ነገ የ100 ዓመቷ የእድሜ ባለጸጋ እናቱ ሴሌስቴ አራንቴስ በሚኖሩበት ሳንቶስ ከተማ የአስክሬን ሽኝት ስነ ስርዓት ተደርጎ በዕለቱ ቤተሰቦች እና የቅርብ ወዳጆቹ ብቻ በተገኙበት ቀብሩ እንደሚፈጸም የኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።

ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ኤድሰን አራንቴስ ዶ ናሲሚዬንቶ ፔሌ ባሳለፍነው ሳምንት በ82 ዓመቱ በአንጀት ካንሰር ሕመም ሕይወቱ ማለፉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም