ምሁራን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ለሀገር ግንባታው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው-ዶክተር በለጠ ሞላ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን በጥናትና ምርምር በመታገዝ ለሀገር ግንባታው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት አለባቸው-ዶክተር በለጠ ሞላ

ሮቤ (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 ምሁራን በጥናትና ምርምር ታግዘው ለሀገር ግንባታው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የመደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ ጠየቁ።
ዶክተር በለጠ ይህን ያሉት በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአገር ግንባታ የምሁራን ሚና በሚል መሪ ሀሳብ ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት ውይይት በተጀመረበት ውቅት ነው።
በውይይቱ ላይ የዩኒቨርስቲው ምሁራን እና የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች አመራሮች የሚሳተፉበት መሆኑም ታውቋል።
ዶክተር በለጠ በዚሁ ጊዜ ምሁራን በጥናትና ምርምር ታግዘው ለሀገር ግንባታው የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ምሁራን በሚያካሄዱት ችግር ፈቺ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎቶት ስራዎችን በማጠናከር ለአገር ግንባታ ሂደት አሻራቸውን እንዲያኖሩ ውይይቱ ጥሩ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

''ምሁራን በአገረ መንግስት ግንባታ እና በአገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር የማይተካ ሚና አላቸው'' ያሉት ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ናቸው።
“ይህን ኃላፊነታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት በመወጣት አገሪቱን ወደ ከፍታ ለማሻገር መረባረብ ይገባቸዋል” ነው ያሉት።

ምሁራን ሁሉን አቀፍ የሰላም፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ዕውን እንዲሆን አገሪቷን በእውቀትና በእውነት መደገፍ እንዳለባቸውም ዶክተር በቂላ ጨምረው ገልጸዋል።
ምሁራን የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያግዙ የጥናትና ምርምር ስራዎችን አጠናክሮ ከማስቀጠል በተጨማሪ በአገረ መንግስት ግንባታ ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡም ተጠይቋል።