በቤተሰብ ላይ የሚሠራ ሥራ ለሀገራዊ አንድነትና የሰላም ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ - ኢዜአ አማርኛ
በቤተሰብ ላይ የሚሠራ ሥራ ለሀገራዊ አንድነትና የሰላም ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23/2015 (ኢዜአ) በቤተሰብ ላይ የሚሠራ ሥራ ለሀገራዊ አንድነትና የሰላም ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ገለጹ።
በቤሰብና በማህበራዊ ጉዳይዮች ላይ የሚሠራው ያሜንት ኢቨንትስ በ2005 ዓ.ም በየሺህ ጋብቻ ትዳር እንዲመሰርቱ ያደረጋቸው ጥንዶች የ10ኛ ዓመት የጋብቻ ክብረ-በዓላቸውን አክብረዋል፡፡
የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶችና እሴቶች በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ባስተላለፉት መልእከት እምቅ ሃብቶቻችንን መጠቀም አለብን፤ የሚያምሩ ባህሎቻችንን ከተደበቁበት በማውጣት ለዓለም ማሳየት አለብን ማለታቸው ይታወሳል።

በመሆኑም እምቅ ሃብቶችንና እሴቶችን በማጉላት ማስተዋወቅና መጠቀም አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በሰፊው እየተሰራበት ይገኛል።
በ2005 ዓ.ም በየሺህ ጋብቻ ትዳር እንዲመሰርቱ ያደረጋቸው ጥንዶች የ10ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን ሲያከብሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በስፍራው በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም በቤተሰብ ላይ የሚሠራ ሥራ ለሀገራዊ አንድነትና የሰላም ግንባታ ሂደት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን ገልጸዋል።
በቤተሰብ መፍረስ ምክንያት የሚመጡ ስጋቶችን ለመከላከል በትዳርና በቤተሰብ አያያዝ ላይ ቀድሞ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት።
በ2005 ዓ.ም በየሺህ ጋብቻ ፕሮግራም 1000 ጥንዶችን በመዳር የተለየ ዝግጅት መካሄዱን በማስታወስ በወቅቱ የተጋቡ ጥንዶች በፍቅርና በመተሳሰብ ለ10 ዓመታት መቆየታቸው የሚደነቅ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ የ2005 ዓ.ም ተጋቢዎች ትዳር በመሠረቱበት ከተማ ከነልጆቻቸው በመገኘት ለዚህ ደማቅ ክብረ-በዓል በመብቃታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የባህል ብዝሃነትንና የቱሪዝም ፍሰትን የሚያሳድጉ በርካታ ሥራዎችን ቢሮው እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ ባለፉት ዓመታት የተሠሩ የተለያዩ ፓርኮችና የመዝናኛ ሥፍራዎች መሰል ሁነቶችን ለማሰናዳት ምቹ ሆነዋል ነው ያሉት።

የያሜንት ኢቨንትስ መስራችና ባለቤት አቶ አስናቀ አማኑኤል፤ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የሺህ ጋብቻ 2005 ዓ.ም በማሰናዳት የአገሪቷን በጎ ገፅታ ለዓለም ማሳየት መቻሉን አስታውሰዋል።
ከነዚህ መካከል ከ100 የሚበልጡ ጥንዶች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመምጣት የ10ኛ ዓመት የጋብቻ ክብረ-በዓላቸውን ከልጆቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአዲስ አበባ አክብረዋል ነው ያሉት።
በ2015 ሁሉንም የሀገራችንን ክፍሎች ያሳተፈ እና ከአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ 100 ጥንዶች ያካተተ 1000 ጥንዶች የሚሳተፉበትን ልዩ ሁነት እያሰናዳ እንደሆነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ባህሎች እና ጌጣጌጦች እያስተዋወቅን ኢኮኖሚያዊ አቅማችንን ለመገንባት ዝግጀቱ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም የሚካሄደው የሺህ ጋብቻ፣ካርኒቫል እና ኤክስፖ በይፋ የተገለፀ ሲሆን በዚህ ዝግጅት መሳተፍ የሚፈልጉ ጥንዶች ምዝገባም በይፋ ተጀምሯል፡፡
በሸራተን አዲስ በተከሄደው የ10ኛ ዓመት የጋብቻ ክብረ- በዓል ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትርን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡