ምሁራን ለሀገር ግንባታው መሳካት ገንቢ ሀሳቦችን እና የምርምር ውጤቶችን እንዲያቀርቡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን ለሀገር ግንባታው መሳካት ገንቢ ሀሳቦችን እና የምርምር ውጤቶችን እንዲያቀርቡ ተጠየቀ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 ምሁራን በሀገረ መንግስት ግንባታው ገንቢ ሃሳቦችን እና የምርምር ውጤቶችን በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።
"በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምሁራን የምክክር መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው የሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ድረስ ሣህሉ እንደገለጹት፣ በሀገረ መንግስት ግንባታ የምሁራን ሚና ከፍተኛ ነው።

"በአሁኑ ወቅት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሀሳብ ያካተተ ሀገር የመገንባት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
በመሆኑም ምሁራን ለሀገር የሚጠቅም ሀሳብና ምርምሮችን በማቅረብ ምሁራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በሀገር ግንባታ ሂደት ያለምሁራን ንቁ ተሳትፎና ትብብር ብዙ ርቀት መጓዝ እንደማይቻል የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ናቸው።
ኢትዮጵያ በኢኮኖሚውም ሆነ በዲፕሎማሲው መስክ ውጤታማና ተምሳሌት እንድትሆን ምሁራን ያላቸውን አቅም ለአገራቸው አሟጠው በማዋል አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ በሰው ሀብት፣ በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው መስክ ያላትን እምቅ አቅም በአግባቡ ተጠቅማ ጠንካራ ሀገር እንድትሆን በእውቀት የታገዘ ሥራ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ይህ እውን የሚሆነው በአገር ግንባታ ሥራ ምሁራን በጥናትና ምርምር የታገዘ ድጋፍ በማድረግ ሃላፊነታቸውን መወጣት ሲችሉ መሆኑንም አስረድተዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የምክክር መድረክ ዛሬን ጨምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።