የሰላም ስምምነቱ ኢትዮጵያውያን በመነጋገር ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ ነው- የሰላም ሚኒስቴር

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 በመንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያውያን በመነጋገር ችግሮቻቸውን መፍታት እንደሚችሉ በተግባር ያሳየ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴርና በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች "የሰላም ስምምነቱ ለአብሮነታችንና ለዘላቂ ሰላማችን" በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ፤ ኢትዮጵያውን ግጭቶችን በመነጋገር በመፍታት ላይ መሆናቸውን ያሳየ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የሆነች ታላቅ አገር ነች" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለአገር ብልጽግና ሰላምና አብሮነት በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።

"ጀብደኝነት ወደ ግጭት ያመራል፣ ጦርነት ደግሞ በብዙ ጥረት የተገኘውን ሀብት ያወድማል፣ ድህነትን ያስፋፋል በመሆኑም ጥፋት ከሚያስከትሉ ተግባራት በመራቅ ለልማታችን በጋራ መስራት አለብን" ነው ያሉት።

ከዚህ አንፃር የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ታሪክ ግጭትን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት በኩል አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም አንስተዋል።

የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ልምምድ መሆኑን ገልጸው ግጭትና አለመግባባትን በማስቀረት ሁላችንም ለአገራችን ሰላም ቅድሚያ እንስጥ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና እንዲሰፍን ሁሉም የሰላም ስምምነቱን በማጽናት ለሰላምና አብሮነት እንዲሰራም ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ የሰላም ሂደቱንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሚመለከት ሰፊ ምክክር እየተደረገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም