ምሁራን ሁሉን አቀፍ የሰላም፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ዕውን እንዲሆን ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው-ዶክተር ፍጹም አሰፋ - ኢዜአ አማርኛ
ምሁራን ሁሉን አቀፍ የሰላም፣ የልማት እና የብልጽግና ጉዞ ዕውን እንዲሆን ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው-ዶክተር ፍጹም አሰፋ

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ታህሳስ 23/2015 ምሁራን ሁሉን አቀፍ የሰላም፣ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ዕውን እንዲሆኑ የማይተካ ሚናቸውን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለማድረስ ሊረባረቡ እንደሚገባ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ።
ዶክተር ፍጹም አሰፋ ይህን ያሉት ለሁለት ቀናት በአገር ግንባታ እና ወቅታዊ ጉዳዮች የምሁራን ሚናን በተመለከተ ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እና የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች አመራሮች ጋር ያካሄዱት ውይይት ሲጠናቀቅ ነው።
ሚኒስትሯ ምሁራን በአገረ መንግስት ግንባታ እና በአገሪቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል።

"ይህን ኃላፊነታቸውን ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት በመወጣት አገሪቱን ወደ ከፍታ ለማሻገር መረባረብ ይገባቸዋል" ነው ያሉት።
ብቃት ያለው፣ በስነ ምግባር የታነፀ እና አገር ተረካቢ ዜጋ የማፍራት ተግባራቸውን ከማጠናከር ጎን ለጎን ተማሪዎች በአፍራሽ አጀንዳዎች ተጠልፈው ቀጣይ ግባቸው እንዳይሰናከል ማገዝ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
"በተለይ የአገር መሰረታዊ ችግሮች እንዲፈቱና ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የብልጽግና ጉዞው እውን እንዲሆን የተቀናጀ የምሁራን ሚና መጎልበት አለበት" ብለዋል ሚኒስትሯ።
እነዚህን ተግባራት ለማጠናከር እና ምሁራን ተልዕኳቸው በሰመረ መንገድ እንዲከናወን ለሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት ጥሩ መደላደል የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው የኢትዮጵያን የሰላም፣ የልማትና የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ምሁራን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሃላፊነታቸውን በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
"በተለይ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ኢትዮጵያ ከጎረቤትና ከዓለም አገራት ጋር ሁለንተናዊ ግንኙነቷ እንዲጠናከር በማገዝ በኩል ከምሁራን ብዙ ይጠበቃል" ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ አበረታች ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዑባህ አደም ናቸው።
"በቀጣይም ለአገር ግንባታ የሚያግዙና ለትውልድ የሚጠቅሙ የምርምር ተግባራትን ዩኒቨርሲቲው አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
መሰል የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና አመራሮች እንዲሁም ተማሪዎችን የርስ በርስ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
"ምሁራን ለዘላቂ ሰላም እና ለአገር ብልፅግና መረጋገጥ የሚያግዙ የተቀናጁ ሥራዎችን በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ይደረጋል" ሲሉም ዶክተር ዑባህ አመልክተዋል።
በውይይቱ የተሳተፋት ምሁራን በበኩላቸው ውይይቱ አገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተጨባጭ እንዲረዱ ከማድረግ ባሻገር የተጣለባቸውን አገራዊና ተቋማዊ ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት ለመወጣት ያነቃቃቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ ዜና በከተማው የሚገኙ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችና በአገር ግንባታ ላይ ውይይት ማካሄዳቸው ታውቋል።