አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ ነው

141

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 21/2015  ኢትዮጵያ የሕክምና ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት እያደረገች ያለውን ጥረት የሚደግፉ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ መሆኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገለጸ።

ዩኒቨርስቲው ኮቪድ-19 ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖና ሊወሰዱ የሚገቡ ትምህርቶች ላይ ውይይት አድርጓል።

ለውይይት መነሻ ጹሁፍ ያቀረቡት የዩኒቨርስቲው የልህቀት ማዕከል የሆነው የ"CDT-Africa" ኃላፊ ፕሮፌሰር አበባው ፈቃዱ  ወረርሽኙ በምጣኔ ሃብት፣ማህበራዊና በሥነ-ልቦና ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ዘርዝረዋል።

አዳዲስ ሃሳቦችንና የፈጠራ ውጤቶችን በማውጣት ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት በወረርሽኙ ወቅት የተወሰደ ልምድ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ኮቪድ-19ን ጨምሮ ለሌሎች በሽታዎች በህክምና ግብዓቶችና መድሃኒቶች እራስን ለመቻል እያደረገች ያለውን ጥረት ለመደገፍ ሙያተኞችን በማሰልጠንና ምርምሮችን በማድረግ እየሰራ ይገኛል።

ዩኒቨርስቲው በመድሃኒቶች ላይ ብቻ ሳይሆን የበሽታ መመርመሪያ መሣሪያዎችም ጭምር በአገር ውስጥ ለማምረት የሚረዱ ምርምሮችንም እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ኢትዮጵያን እንዲሁም አፍሪካ በህክምና ግብዓት እራሳቸውን እንዲችሉ አስፈላጊውን ሥልጠናና ምርምር በማድረግ እንደሚደግፍም ኃላፊው ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ኮቪድ-19 እንዲሁም ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተደረጉ ጥናትና ምርምሮች 50 በመቶ የሚሆኑት ኮቪድ-19ን የተመለከቱ እንዲሁም ከኮቪድ ጋር የተያያዙ 14 ቴክኖጂዎችን ማውጣቱን አስረድተዋል።

ዩኒቨርስቲው በቀጣይም በህክምና ላይ የሚያደርገውን ጥናትና ምርምር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።

በሽታው አሁንም የአለም ሥጋት ሆኖ በመቀጠሉ ትብብርን ማጠናከርና አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተማላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም