የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ የመጣበት ሰላምን ለማጽናትና እርስ በርስ ያለንን ሃሳብና ስሜት ለመካፈል ነው -የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ

139

ታህሳስ 17/2015 (ኢዜአ) የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ የመጣበት ሰላምን ለማጽናትና እርስ በርስ ያለንን ሃሳብና ስሜት ለመካፈል ነው ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በአፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የተመራ የፌደራል መንግስት ልዑክ ዛሬ በመቀሌ ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት እያሳዩት ያለው በሳል አመራር የሚደነቅ መሆኑን የህወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናግረዋል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ሚኒስትሮችን፣ የመንግስት መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አመራሮችን፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮችን ያካተተ ሲሆን፤ መቀሌ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት የልዑካን ቡድኑ ወደ መቀሌ የመጣበት ዓላማ ሰላምን ለማጽናትና እርስ በርስ ያለንን ሃሳብና ስሜት ለመካፈል ነው ብለዋል፡፡

የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብ ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስም በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የባንክ፣ የመብራት፣ የቴሌኮም ፣የመንገድ፣ የአየር መንገድና መሠል አገልግሎቶችን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስጀመር ተቋማቱን የሚመሩ አመራሮቹ በልዑካን ቡድን ውስጥ ተካተው መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

የዛሬው ዕለት ትልቅ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ያሉት አፈጉባኤው፤ አገልግሎቶችን ለማስጀመር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም