የሴቶች እና ሕጻናትን ጥቃት ለማስቆም በተደራጀ አግባብ መስራት እንደሚገባ ተገለጸ

130

ወልዲያ (ኢዜአ) ታህሳስ 17/2015 "በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተደራጀ መንገድ መስራት ይገባል" ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡመድ ገለፁ።

ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች አገልግሎት እንዲሰጥ በወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የተገነባው የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ሥራ ጀምሯል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ዛሬ ማዕከሉን መርቀው አገልግሎት ሲያስጀምሩ እንዳሉት፣ በደረሰባቸው የአስገድዶ መድፈር ጥቃት አካላዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና የጤና ቀውስ የገጠማቸው ሴቶችና ሕጻናት በርካታ ናቸው።

እነዚህ ወገኖች በደረሰባቸው ቀውስ ቤት ዘግተውና ራሳቸውን ደብቀው መቀመጣቸውንም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

እነዚህ ዜጎች ካሉበት አስከፊ ሁኔታ ወጥተው ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ መረባረብ እንደሚገባ ጠቁመው፤ "ዛሬ ለአገልግሎት የበቃው የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ይህንን የሚያግዝ ነው" ብለዋል።

ራሳቸውን ደብቀው በሕመም የሚሰቃዩ ወገኖች ወደ ማዕከሉ መጥተው ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ባለሙያዎች፣ የፍትህ አካላት እና ህብረተሰቡ የበኩላቸውን እንዲወጡም ወይዘሮ አለሚቱ አሳስበዋል።

በሴቶችና ህጻናት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

"ለዚህ ስኬታማነት ሚኒስቴሩ ተገቢውን እገዛ ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ ነው" ሲሉም አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫው በዩኒሴፍ ድጋፍ መገንባቱን ጠቁመዋል።

"በደረሰባቸው የመደፈር ጥቃት ራሳቸውን አግለው የተቀመጡ ወገኖችን የስነ-ልቦናና የህክምና አገልግሎት በመስጠት ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይኖርብናል" ሲሉም ተናግረዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃትና መደፈር ከሰብዓዊና አካላዊ ጉዳት ባሻገር በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል።

በዩኒሴፍ የተጀመረውን ሥራ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።

የዩኒሴፍ ተወካይ ወይዘሮ ምዕራፍ አበበ እንዳሉት፣ ዛሬ ከተመረቀው የወልዲያ የአንድ ማዕከል አገልገሎት መስጫ በተጨማሪ በባህር ዳርና ደሴ ከተሞች ተመሳሳይ ግንባታ በማከናወን ተጎጂዎች አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከዩኒሴፍ በተገኘ 7 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነበው ማዕከል ስምንት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የተለያዩ የሕክምና መርጃ መሳሪያዎችም ተማልተውለታል።

በማዕከሉ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የፌደራል አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም