አረምና ተባይ የሚከላከሉ የእፅዋት ዝርያዎች ላይ የዘር ብዜት ይካሄዳል-የወሎ ዩኒቨርሲቲ

149
ደሴ መስከረም 20/2011 የአቀንጭራ አረምና የአገዳ ቆርቁር ተባይ በሽታዎችን በመከላከል ውጤታማ የሆኑ ሁለት የእፅዋት ዝርያዎች የዘር ብዜት እንደሚያካሂድ የወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ ዝርያዎቹን የማስፋፋት ኃላፊነቱን አልተወጣም ብሏል። ዩኒቨርሲቲው በቤተ- ሙከራ የታገዘውን የዘር ብዜት  የሚያካሂደው በሽታዎቹን የሚከላከሉ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የእጽዋት ጥበቃ መምህርና የምርምሩ አስተባባሪ አቶ ሰይድ ሀሰን ለኢዜአ ገልጸዋል። ብዜቱ የሚካሄደው ከአራት ዓመታት በፊት በምርምር በወጡና በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በ135 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሞክረው ውጤታማ በሆኑ የእፅዋት ዝርያዎች ላይ ነው። “ 'ሳቢ'ና 'ገፊ' በሚል ስያሜ የተሰጣቸው የእፅዋት ዝርያዎች በማሽላ ሰብል ላይ የሚከሰት የአገዳ ቆርቁር ተባይና የአቀንጭራ አረምን በመከላከል ውጤታማ ሆነዋል" ብለዋል ። በተጨማሪም በማሳ ውስጥ የአፈር ለምነትን በመጨመርና ለእንስሳት መኖነት በመዋል ምርት ለመጨመር እንደሚያስችሉም ገልጸዋል ። አስተባባሪው እንዳሉት የእፅዋት ዝርያዎቹ በሚያመነጯቸው ሽታ አዘል ንጥረ ነገር ተባይና አረሙን መከላከል አስችለዋል። "በተለይም 'ገፊ' የተባለው ሃረጋማ ተክል  ናይትሮጂን የማመንጨት ተፈጥሯዊ አቅም ስላለው ዩሪያ ማዳበሪያን በመተካት ለምርታማነት እድገት አስተዋጽኦ እንዳለው ተረጋግጧል" ብለዋል ። የዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት ምርምር ማድረግ፣ የምርምሩን ውጤትን ማስተዋወቅ፣ ስልጠና መስጠትና ሙያዊ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን አስረድተዋል።ዩኒቨርሲቲው ዘላቂ ልማት መካነ ጥናትና ማክናይት ፋውንዴሽን ከተባሉ ድርጅቶች ባገኘው 5ሺህ ዶላር ድጋፍ የዘር ብዜቱ እንደሚየከናውን አስተባባሪው አስረድተዋል ። “ዩኒቨርሲቲው  የእፅዋት ዘርያዎቹን ባስተዋወቀበት የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን  የግብርና ዘርፉ ቴክኖሎጂውን ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች ለማስፋፋት ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም”ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይም ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባውም አሳስበዋል። የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አበራ ይመር መምሪያው ከክልሉ ግብርና ቢሮና ከሚመለከታቸው ከፌደራል ተቋማት ጋር በመነጋገር ቴክኖሎጂውን በሌሎች አርሶ አደሮች ማሳ ለማስፋት ጥረት እንደሚያደርግ አመላክተዋል፡፡ የእፅዋቶቹን ዘር ለማግኘትና ለማምረት ከፍተኛ ወጭ የሚጠይቅ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ታግዞ ዘሩን በአገር ውስጥ ማምረት ከቻለ፤ አቀንጭራ አረምና ግንደ ቆርቁር ተባይን ለመከላከል የተጀመረው ጥረት ውጤታማ እንደሚሆን ቡድን መሪው አስታውቀዋል። በዞኑ ዳዋ ጨፋ ወረዳ በደኖ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አደም አህመድ ከዚህ ቀደም በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ  የሚዘሩት ማሽላ በአቀንጭራና በአገዳ ቆርቁር ስለሚጠቃ የሚያገኙት ምርት ከአምስት ኩንታል በልጦ እንደማያውቅ አስታውሰዋል። ካለፈው አመት ጀምሮ የእፅዋት ዘርያዎቹን በመጠቀም አረሙንና ተባዩን መከላከል በመቻላቸው በተለይም በዘንድሮ መር በተመሳሳይ ማሳ ላይ ከዘሩት ማሽላ 20 ኩንታል ምርት አግኝተዋል ። “የሳርና ሀረግ ዝርያዎቹን ለከብቶች መኖነት እየተጠቀምኩ ነው” ሲሉ አርሶ አደር አደም ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም