"በየጊዜው ከሚፈጠሩ የግጭት አጀንዳዎች ጀርባ ያለው ሴራ የኢትዮጵያን ልማት ማስቆም ነው፤ ይህንን ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም"

288

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 14/2015 "በየጊዜው ከሚፈጠሩ የግጭት አጀንዳዎች ጀርባ ያለው ሴራ የኢትዮጵያን ልማት ማስቆም ነው፤ ይህንን ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ የተገነባው የዳቦ ፋብሪካ በተመረቀበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

ፋብሪካው በቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት አማካኝነት፥ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ እና ሂቤይ ፒንግል ማሽነሪስ አጋርነት የተገነባ ነው።

ፋብሪካው በቀን 300 ሺህ ዳቦ እና 42 ቶን ዱቄት የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፤ በዋናነት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት የዳቦ ፋብሪካን ጨምሮ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ እያከናወነ ያለውን ስራ አድንቀዋል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሚከናወኑ ስራዎች የነገ አገር ተረካቢ ትውልድን ታሳቢ ያደረጉ ስለመሆናቸውም ነው የተናገሩተ፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ9 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ-ግብር ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የሚገነቡ የዳቦ ፋብሪካዎች ይህን ስራ በማገዝ ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም አየር መተንፈስ የሚያስችሉ እድሎች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር በሰላም ለመፍታት የተደረሰውን ስምምነት ለአብነት አንስተዋል፡፡

ዜጎች ይህ እድል እንዳይበላሽ ይልቁንም ይበልጥ እንዲሰፋ ሊሰሩ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሚከናወኑ ስራዎች የሁሉንም ትብብር የሚጠይቁ መሆናቸውንም አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

"በጥላቻና መገፋፋት ማንም ማሸነፍ አይችልም፤ ለኢትዮጵያውያን የሚበጀው አብሮነትና ትብብር ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን አንዳችን ለሌላችን ግማሽ አካል መሆናችንን ተገንዝበን አብሮነታችንን ይበልጥ ማጠናከር አለብን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡

ይህን በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር ይገባል ብለዋል፡፡

የግጭት አጀንዳ በመቀስቀስ መንግስት በሌብነት ላይ የጀመረውን ዘመቻ ለማስቆም የሚሞክሩ ኃይሎች መኖራቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን በሙስና እና የተደራጀ ሌብነት ላይ የተጀመረው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያን ሌብነት ክፉኛ እየጎዳት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ሌብነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ስራዎች አካል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም