በምሥራቅ ወለጋ ዞን ዛሬ ጠዋት በደረሰው የመኪና አደጋ የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

96
ነቀምቴ መስከረም 20/2011 በምሥራቅ ወለጋ ዞን ዛሬ ጠዋት በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ10 ሰዎች ህይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ሶስት ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የትራፊክ ደህንነት ዲቪዥን ሃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ፍሮምሣ ሰለሞን እንዳስታወቁት አደጋው የደረሰው 13 ሰዎችን አሳፍሮ ከነቀምቴ ወደ ጅማ አርጆ ወረዳ ሲጓዝ የነበረ ሚኒባስ ከበደሌ ወደ ነቀምቴ ሲገዝ ከነበረ የጭነት መኪና ጋር በመጋጨቱ ነው። የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-40401 ኦሮ የሆነው ይሄ ሚኒባስ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-80850 ኢት ከሆነ ትራከር የጭነት መኪና ጋር በሌቃ ዱለቻ ወረዳ አሌ ቀዊሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲደርስ በመጋጨቱ ጉዳቱ ሊደርስ መቻሉን ተናግረዋል። ከባድ የመቁሰል  አደጋ የደረሳባቸው ሶስት ተሣፋሪዎች ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታል ተወስደው የሕክምና ዕርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸው የማቾቹ አስከሬንም ወደ ቤተሰቦቻቸው መላኩን አስታውቀዋል። የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን የገለጹት ኢንስፔክተር ፍሮምሳ ለጊዜው የተሰወሩት የሁለቱ መኪኖች አሽከርካሪዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም