በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎችን የመሰረተ ልማት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው--አቶ ሽመልስ አብዲሳ

72

ጎባ( ኢዜአ )ታህሳስ 13/2015 በኦሮሚያ ክልል የቱሪስት መዳረሻዎች የሚስተዋለውን የመንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት ችግሮች በመፍታት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የሮቤ-ጎሮ-ሶፍ ዑመር-ጊኒር የመንገድ ማጋጠሚያ የአስፋልት መንገድ ኘሮጀክት ግንባታ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።

የግንባታ ስራውን ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት የክልሉ መንግስት የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትኩረት እተሰራ ይገኛል።

በተለይም በሚገኙ በቱሪስት መዳረሻዎች አካባቢ የሚስተዋለውን የመንገድ መሰረተ ልማት ችግር በመፍታት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ ትላልቅ ዋሻዎች አንዱ የሆነውና ድንቅ የቱሪስት መዳረሻ የሶፍ ዑመር ዋሻን መሰረት በማድረግ ዛሬ የተጀመረው የመንገድ ፕሮጀክትም አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

የክልሉ መንግስት ሁለቱን የባሌ ዞኖችን የግብርና ምርት፣ የቱሪዝምና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ጥረቱ እንዲሰምር መንገዱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የክልሉ ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ገልጸዋል።


የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው "የባሌ አርሶ አደሮች ትናንት ለነጻነትና ለእኩልነት ያደረጉት ትግል ዛሬ ፍሬ አፍርቷል" ብለዋል።


የመንገዱ መንገባት በአካባቢው የሚገኙ እምቅ የኢኮኖሚ አቅሞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

መንገዱ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ህዝቡ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን ያስችላል ያሉት ሚኒስትሯ፤ መንግስት የህዝቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ እንደሚመልስም የባሌው መንገድ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው፤ መንግስት የመንገድ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ ነው ብለዋል።

የሮቤ-ጎሮ-ሶፍ-ዑመር-ጊኒር መገንጠያ መንገድ አካባቢው የሚታወቅበትን የግብርና ምርት ወደ መሃል ሀገር ተደራሽ ለማድረግና የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ኢንጂነር ሀብታሙ እንዳሉት፤ የመንገዶች አስተዳደር በየዞኖቹ እየተገነቡ የሚገኙ መንገዶች በተያዙላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ 29 የፕሮጀክት ማኔጅመንት ቢሮ ከፍቶ እየተከታተለ ይገኛል።

በባሌ አካባቢ እየተካሄዱ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የሚከታተል ቢሮም ሮቤ ላይ መከፈቱን ጠቁመዋል።

ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ የኢትዮጵያ መንግስት ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን አመልክተው፤ 120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይኸው መንገድ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቅ አስታውቀዋል።

"ሲ ሲ ሲ ሲ" የተባለው የቻይና የመንገዱ ተቋራጭ ተወካይ ታኦ ሆእ፤ ድርጅቱ ለዘመናት ባከበተው ልምድ በመጠቀም ፕሮጀክቱን በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንደሚያጠናቅቅ ተናግረዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ሃጂ አሎ ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ የትውልዶች ጥያቄ መልስ በማግኘቱ ተደስተናል ብለዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬት የሚጠበቅብንን እንወጣለን፤ መንገዱ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድጋፋችን አይቋረጥም ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም