ኢትዮጵያ ታምርት ክልል አቀፍ ንቅናቄ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው

92

ሐዋሳ(ኢዜአ)  ታህሳስ 13 ቀን 2015 በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዘው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 2ኛ ዙር ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የሲዳማ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻዎች ተገኝተዋል።

በሲዳማ ክልል ባለፈው አንድ ዓመት በተካሄደ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና የውጭ ምንዛሬን ማሳደግን ጨምሮ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ስራ ውጤት እንደታየበትም ተመላክቷል።

በዚህም ከአንድ አመት በፊት በክልሉ 865 የነበሩ የአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ቁጥር ባለፈው አንድ ዓመት በተሰራው የንቅናቄ ስራ 1 ሺህ 58 መድረሱን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተገኙ ተሞክሮዎችና ተግዳሮቶች ላይ ያተኮረ ሰነድና ክልሉ ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት እያዘጋጀ ባለው የአምራች ኢንዱስትሪው ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂክ ፕላን ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም