ለታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ702 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰበሰበ

155

ታኅሳስ 13/2015(ኢዜአ) በበጀት ዓመቱ አራት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከ702 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለጸ።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የሕዝቡ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በ2015 በጀት ዓመት ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙ ይታወቃል፡፡

የጽህፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም፤ በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ባለፉት አራት ወራት ብቻ 702  ሚሊየን 709 ሺህ  ብር ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥና በዳያስፖራ ቦንድ ግዥና ስጦታ፣ በ8100 A የጽሑፍ መልዕክት እንዲሁም በሌሎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መንገዶች ገቢው መሰብሰቡን አብራርተዋል።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡

በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ እውን መሆን የሚያሳዩትን ድጋፍና አጋርነት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን ለሕብረተሰቡ በማስተዋወቅ በኩል መገናኛ ብዙኃን የበኩላቸውን እገዛ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡

የሕዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን፤ ከ70 በላይ ደሴቶች የሚፈጠሩበት በመሆኑም በቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት አገራዊ ፕሮጀክት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም