ሼሕ አሊ አላሙዲን በቅርቡ ከእስር እንደሚለቀቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተናገሩ

147
አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 ሼክ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን በቅርቡ ከእስር ተለቀው ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ተናገሩ። ዶክተር አብይ ሰሞኑን ወደ ሳዑዲ አረቢያ በማቅናት ስኬታማና በብዙ መልኩ መግባባት ላይ የተደረሰበት የስራ ጉብኝትና ምክክር እንዳደረጉ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር እስረኞችን ለማስፈታት ባደረገው ዲፕሎማሲያዊ ምክክር በአገሪቱ በህግ ጥላ ስር የነበሩ 1ሺህ ኢትዮጵያውያንን አስፈትተዋል። "የሼሕ አላሙዲን መታሰር በዓለም ላይ ያሉ ዳያስፖራዎች ሁሉ አጀንዳ መሆን አለበት" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የአንዱ ኢትዮጵያዊ መታሰር የሌላው መታሰር፤ የአንዱ መፈታት የሌላው መፈታት ነው' በማለት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ሀብታም ደሃ ሳይል በሳዑዲ በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎችን ለማስፈታት ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር አብይ ሼህ አሊ አላሙዲን በቅርቡ ለአገራቸው እንደሚበቁ ገልጸዋል። 'የሚጎሳቆል ዜጋ፣ የሚታሰር ዜጋና የሚናቅ ዜጋ ያለው አገር የሕዝቦቹ ውጤት ነውና የተናቀ ከመሆን አይድንም' ያሉት ዶክተር አብይ አሕመድ አንድም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መታሰር እንደሌለበት ተናግረዋል። ዶክተር አብይ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር ባደረጉት ውይይት ከእስር እንዲለቀቁ ከተደረጉ 1ሺህ ኢትዮጵያውያን መካከል 690ዎቹ ትናንት ምሽት አገራቸው መግባታቸው ይታወቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም