በደቡብ ክልል ሴቶች ሊግ የሚተገበር የ"ሌማት ትሩፋት" መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው

138

ሆሳዕና:- ታህሳስ 10/2015 (ኢዜአ ) በደቡብ ክልል በሴቶች ሊግ አደረጃጀቶች ተፈጻሚ የሚሆን ክልል አቀፍ የ"ሌማት ትሩፋት" መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በሀድያ ዞን ሌሞ ወረዳ በሹርሞ ዊጥቢራ ቀበሌ እየተካሄደ ነው።

"የተመጣጠነ ምግብ እመገባለሁ ሁሉንም ከደጄ አመርታለሁ" በሚል መርህ የሚካሄደው መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርአት እየተካሄደ ነው ።

በሊጉ በሚተገበረው መርሃ ግብር በክልሉ የሚገኙ ከ833 ሺህ በላይ አባላት እንደሚሳተፉ ተመላክቷል ።

በመርሀ ግብሩ በአባላቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የጓሮ አትልክልትና ቅመማ ቅመም ልማት ፣ ንብ ማነብ፣ እንስሳት ማድለብ፣ የወተት ተዋጽኦ ዝግጅት፣ ዶሮ እርባታ እንደሚገኙበት ተገልጿል።

አባላቱ በመርሀ ግብሩ በመሳተፍ የግብርና ውጤቶችን ከቤት ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድጉበት መሆኑም ተመላክቷል ።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ክላስተር  አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩርና የደቡብ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪና የፖለቲካና ርእዮተዓለም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ተገኝተዋል ።

እንዲሁም የክልሉ የሴቶች ሊግ ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ ሙኒርን ጨምሮ ከሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የሊጉ አመራሮች ተሳትፈዋል ።

የስነ ስርአቱ ተሳታፊዎች በሆሳዕና ከተማ ተደራጅተው በወተት ተዋጽኦ ዝግጅት የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም