ማህበራዊ ሚዲያን ለአገራዊ አንድነትና ለሌሎች በጎ ተግባራት ላዋሉ እውቅና ሊሰጥ ነው

77
በህር ዳር መስከረም 19/2011 ማህበራዊ ሚዲያን ለአገራዊ አንድነት ማጠናከሪያና ለሌሎች በጎ ተግባራት ላዋሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዕውቅና እንደሚሰጥ “ጣና ሽልማት” የተሰኘ በጎ አስድራጎት ድርጅት ገለጸ። ድርጅቱ ትናንት በሰጠው መግለጫ እንደገለጸው ለሁለተኛ ጊዜ የተዘጋጀው ሽልማት የነጻ ትምህርት እድልና ማበረታቸዎችን የያዘ ነው። የሽልማት ስነ ስርዓቱ አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ምህረት እንደገለጹት የሽልማቱ ዓላማ የማህበራዊ ሚዲያን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ የህብረተሰቡን አስተሳሰብና አመለካከት በመልካም ለመለወጥ እንዲውል ማድረግ ነው። በተጨማሪም የበሰለና አገራዊ ስሜት የሚሰማው ማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም ማህበረሰባዊ ኃላፊነትን የሚያስቀድሙ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎችን ለማበረታታትና ተተኪዎችን ለማፍራት መሆኑን አስረድተዋል። ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው ሽልማት ተሸላሚ የሚሆኑት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ነጻ የትምህርት እድልና ድርጅቱ ያዘጋጀው ሽልማት ይበረክተላቸዋል። "የሽልማት ስነስርዓቱን በፍትሃዊነት ለማካሄድም የተለያዩ የሙያ ስብጥር ያላቸው ግለሰቦችን የያዘ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሰራ ይገኛል" ብለዋል። ኮሚቴውም  “ጣና አዋርድ” በተሰኘ የፌስቡክ ገጽ ከ49 ሺህ ድርጅቶችና ግለሰቦች መረጃ በጥቆማ ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸው ከነዚህ ውስጥ 100 ተጽኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና ድርጅቶች ለመጨረሻ ውድድር መቀረባቸውን አስረድተዋል። አቶ ሰለሞን እንዳሉት 16 ተሸላሚዎችን ለመለየት የተመለመሉት 100 እጪዎች ከወገንተኝነትና ዘረኝነት የጸዳ ሐሳብ ሲያንሸራሽሩ የነበሩና በማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች አማካኝነት በገለልተኛ አጣሪዎች የተመረጡ ናቸው። መስከረም 26ቀን 2011ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ ብሉ ናይል ሆቴል በሚካሄደው የእውቅና ስነስርዓት የሚመረጡት 16 ግለሰቦችና ድርጅቶች ተሸላሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል። ባለፈው ዓመት የጣና አዋርድ ተሸላሚ የሆኑ 11 ግለሰቦች በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የነጻ ትምህርት እድል አግኝንተው በመማር ላይ እንደሚገኙም አስታውሰዋል። በሽልማት መርሀግብሩ ላይ “ጣና ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ሚዲያ ጉባኤ” በሚል ርዕስ የመወያያ ጽሁፍ ቀርቦ ተሳታፊ እንግዶች ውይይት እንደሚያደርጉም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም