የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመሠረታዊ ክህሎቶች ላይ መስራት ይገባል- ጥናት

323

አዲስ አበባ ታኅሳስ 06/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በተማሪዎች መሰረታዊ ክህሎቶች ላይ መሥራት እንደሚገባ ጥናት አመለከተ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በመሆን ላለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት ላይ ያደረገው ጥናት ይፋ ሆኗል።

ጥናቱ በስምንት ክልሎች 168 የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በሚገኙ ዘጠኝ ሺህ ተማሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ነው የተካሄደው።

ይህንንም ተከትሎ 67 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆኑ የ2ኛ ክፍል ተማሪዎችና 51 በመቶ የሚሆኑ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች ማንበብና መጻፍ እንደማይችሉ ተጠቅሷል።

ጥናቱን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትምህርት ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር በላይ ሃጎስ ጥናቱ በርካታ መልካም ጎኖችን ለይቷል ብለዋል።

ለአብነትም ትምህርትን ከማዳረስ አንጻር ስኬታማ ተግባራት መከናወኑን ገልጸው በጥራት በኩል አሁንም ችግሮች መስተዋላቸውን ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸዋል።  

በተለይም የማንበብና የመጻፍ ክህሎት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ተከታታይነት ያለው ሥራ መሥራት እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል ነው ያሉት።

የማንበብና መጻፍ፣ ሂሳብ ማስላትና የተረጋጋ ሥነ-ልቦና እንዲሁም መልካም ማኅበራዊ መስተጋብር የመሰሉ መሰረታዊ ክህሎቶች ላይ በቅድመ መደበኛ እንዲሁም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል በትኩረት መሥራት እንደሚገባና በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ተናቦ የመሥራት ችግሮች ላይ መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባ ጥናቱ አመላክቷል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በጥናቱ ግኝት በጦርነትና በኮቪድ ምክንያት የተማሪዎች የሂሳብ ችሎታ 15 በመቶ መቀነሱን ገልጸው ያም ሆኖ መንግሥት በአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ላይ የሚተገበረው መርሃ ግብር ችግሩ የከፋ እንዳይሆን አስተዋጽኦ ማድረጉንም ነው የጠቆሙት።

በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ አሰራሮች እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ተግባራዊ አለመደረጉ ለትምህርት ጥራት መጓደል ሌላኛው ምክንያት መሆኑ አስረድተዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መንግሥት የተለያዩ ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው በጥናቱ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችንም ለፖሊሲ ግብዓትነት እንደሚጠቀማቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በጦርነትና ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ሳይጨምር ከቅድመ መደበኛ እስከ 12 ክፍል ከ26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም