ለህዝቦች ይበልጥ መቀራርብ እሰራለሁ- በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር

96
አዲስ አበባ መስከረም 19/2011 የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦችን ይበልጥ የሚያቀራርቡ ሥራዎችን በትኩረት እንደሚሰሩ በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ። አምባሳደር ሬድዋን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ባህል፣ ቋንቋንና በርካታ እሴቶችን የሚጋሩና በብዙ መልኩ የሚተሳሰሩ በመሆኑ ለጋራ ተጠቃሚነታቸው እንደሚሰሩ ገልፀዋል። ቀደም ሲል በአየርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በቅርቡ በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ በኤርትራ የተከፈተውን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ሥራ ለማስጀመር በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው። ከ20 ዓመታት በኋላ በኤርትራ የኢትዮጵያ ባለ-ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሆነው በመሾማቸው የተሰማቸውንም ድስታም ገልፀዋል። አምባሳደር ሬድዋን የሁለቱ አገራት ህዝቦችን ይበልጥ በሚያቀራርቡ እና የጋራ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በትኩረት እንደሚሰሩም ነው የገለፁት። የሁለቱ አገራት መሪዎች ባደረጉት ስምምነት ሁለቱም የዘጓቸውን ኤምባሲዎች ዳግም ለመክፈት በተስማሙት መሰረት ኤምባሲዎቻቸው ወደ ሥራ ገብተዋል። በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረው ሰላም፣ የአየርና የየብስ ትራንስፖርት መጀመር እና የወደቦች አጠቃቀም ለሁለቱ አገራት ህዝቦች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ብሩህ ተስፋ ፈጥሯል።                        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም