በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በጦርነቱ የተጎዱ በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም ያገኛሉ- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

160

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 4/2015 በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በጦርነቱ የተጎዱ በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት በድጋሚ እንዲያገኙ የሚያስችል ከፍተኛ የመልሶ ግንባታ ስራ እንደሚከናወን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል።

መንግስት የሰላም ስምምነቱን በመተግበር በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም የማስጀመር ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንዳሉት የሰላም ስምምነቱን ተከተሎ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶች በመጠገን ዳግም አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው።

በዚህም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው የነበሩ  በርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መልሰው እንዲያገኙ ተደርጓል ነው ያሉት።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው የቆዩት የእንዳባጉና፣ የሰለኽላኻ፣ የጨርጨር ከተሞች እና የርብሀ አዲስ ቅኝ ቀበሌ ዛሬ በድጋሚ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸውንም ነው ያነሱት።

መሰረተልማቱን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በመደበኛው ከወራት የበለጠ ጊዜን የሚጠይቅ ቢሆንም መንግስት በያዘው ቁርጠኝነት በጥቂት ቀናት ውስጥ ውጤታማ ስራ ማከናወን ተችሏል ነው ያሉት።

ለዚህም የኤሌክትሪክ ጥገና ባለሙያዎችና አመራሩ የ24 ሰዓት የጥገና ስራ ላይ ማተኮራቸውን ጠቅሰዋል።

አስፈላጊ ግብአቶችን አስቀድሞ በማዘጋጀትና ግብረኃይል በማቋቋም ጭምር መሰራቱ በአጭር ጊዜ በርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም እንዲያገኙ ማስቻሉንም ገልፀዋል።

በዚህም ከዛሬ ጀምሮ እስከ ቀጣዮቹ ሁለት ቀናት በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም እንደሚያገኙ ጠቁሟል።

የተሰራው ስራ አዲስ መስመር ከመዘርጋት ጋር የማይተናነስ ቢሆንም በህብረተሰቡ እገዛ መልካም ውጤት ሊገኝ መቻሉን ነው ያብራሩት።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ቀናት ማይጨው እንዲሁም በአፋር ክልል ከልዋንና ቢሶበር ከተሞች ጥገና ስራ ተጠናቆ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም ማግኘታቸውን አስረድተዋል።

ሽሬና አካባቢውም ከቀናት በፊት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸውን አንስተው የጥገና ስራ በተጠናቀቀባቸው ሌሎች አካባቢዎች የፍተሻ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ሁመራም የኤሌክትሪክ አገልግሎት በድጋሚ ያገኘች ሲሆን፤ በአቅራቢያዋ ያሉ ከተሞችም በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

ለአብነትም ባዕከር፣ ዳንሻ፣ አብራጅራ፣ ሰሮቃ፣ አዲ ጎሹ፣ አዲ ረመፅና ሌሎችም ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ዝቅተኛና መካከለኛ የመስመር ጥገና እንደተጠናቀቀ በማንሳት።

የጥገና ስራውን ለማከናወን በየአካባቢው ካሉ ባለሙያዎች በተጨማሪ የቴክኒክ ባለሙያዎችንና አመራሮችን ያጣመረ ቡድን መላኩንም አስረድተዋል።

በአፋር በኩል የተላከው ቡድንም ከትናንት ጀምሮ በስራ ላይ ሲሆን አብአላ፣ በርሃሌ፣ ዳሎልና መጋሌ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ የጥገና ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

እስካሁን በዋና ዋና ከተሞች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥገና እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ የገጠር ከተሞችን ጭምር ያማከለ ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም