ኢትዮጵያ የቢግ 5 ዓለም አቀፍ የግንባታ ትርኢት ታስተናግዳለች--የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስቴር

178

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 3/2015 ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት ወር 2015 በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የቢግ 5 ዓለም አቀፍ የግንባታ መድረክ እና ትርኢት እንደምታስተናግድ የከተማና መሰረተ-ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ አስታወቁ ።

በመድረኩ እና በትርኢቱ ላይ ከ170 በላይ ሀገራት እና የዘርፉ ተዋናዮች እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።

በሚኒስትር ጫልቱ ሰኒ የተመራ ልዑክ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ዱባይ በተካሄደው የቢግ 5 ዓለም አቀፍ የግንባታ ትርኢት እና መድረክ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ትርኢቱ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ትልቁ እና ከፍተኛ ተፅእኖ የሚፈጥር መድረክ መሆኑንም ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል።

በቆይታቸውም ለኢትዮጵያ የግንባታ እድገት አቅም መፍጠር የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን መመልከታቸውንና ለኢትዮጵያ የግንባታ ችግሮች መፍትሔ መሆን እንዲችል በቀጣይ በስፋት እንደሚሰራበትም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የቢግ 5 የግንባታ ትርኢት እና መድረክ ከዓለም ዙሪያ የግንባታ ምርቶችን ገዥዎችን እና አምራቾችን የሚያሰባስብ፣ ሰፋ ያለ ትምህርታዊ አጀንዳ የሚቀርቡበት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ኮንፈረንሶች የሚከናወኑበት መድረክ መሆኑንም ጨምረው ጠቅሰዋል፡፡

ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ መንግሥት ሴቶችን ወደ ከፍተኛ አመራርነት በማምጣት ሀገራቸው የምትጠብቅባቸውን እንዲወጡ ዕድል እየፈጠረ ነው ብለዋል።

የትርኢቱ ተሳታፊዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀረቡት ሚኒስትሯ ሴቶች በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ማንኛውንም ሚና መጫወት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

“ቢግ 5” የግንባታ የንግድ ትርዒት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ እና በደቡብ እስያ ትልቁ እና ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው የግንባታ ትርዒት ሲሆን ከዚሁ ጎን ለጎን በግንባታው ዘርፍ ያሉ ሴቶችን የሚያስተዋውቅ መድረክ ነው፡፡

በመጪው ግንቦት ወር ላይ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው ይህን ዓለም አቀፍ መድረክ በተሳካ ሁኔታ ሁኔታ ማከናወን እንዲቻል የዘርፉ ተዋናዮች እና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ የበኩላቸውን አገራዊ ሀላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም