በትግራይ ክልል 3ሺህ ለሚበልጡ የተፈናቃይ ቤተሰብ ልጆች የጽህፈት መሳሪያ ድጋፍ ተደረገ

82
መቀሌ መስከረም 18/2011 በትግራይ ክልል ከሦስት ሺህ የሚበልጡ የተፈናቃይ ቤተሰብ ልጆች መደበኛ ትምህርት እንዲጀምሩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ንግስቲ ወልደሩፋኤል ለኢዜአ እንደገለፁት በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ከተፈናቀሉ 34 ሺህ ዜጎች 6 ሺህ ያህሉ ህፃናት ናቸው። “ከነዚህም ግማሽ ያህሉ በየአካባቢያቸው እንዲማሩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ባደረጉት ድጋፍ የትምህርት ቁሳቁስ እንዲሟሉላቸው ተደርጓል” ያሉት ወይዘሮ ንግስቲ ድጋፉ ቦርሳ፣ ደብተር፤ እስክሪብቶና እርሳስን እንዳካተተ ተናግረዋል። በድጋፉ ላይ ከተሳተፉ አካላት መካከልም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከ120 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትምህርት ቁሳቁስ፣ የክልሉ ውሃ ሃብት ቢሮ 50ሺህ ብር ፤ የትግራይ ልማት ማህበር ደግሞ 16ሺህ ብር ማበርከታቸውን ገልጸዋል። የቀሩ ሦስት ሺህ የሚሆኑ ህፃናት በየአካባቢያቸው ተመዝግበው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ድጋፍ የማድረግ እንቅስቃሴው መጠናከሩን ምክትል ቢሮ ሀላፊዋ አስረድተዋል። በተደረገላቸው ድጋፍ ትምህርት ከጀመሩ ታዳጊዎች መካከል በዓዲ-ሓ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርቱን መከታተል የጀመረው ተማሪ ታከለ ተስፋይ እንዳለው የተሰጠው የጽህፈት መሳሪያ ከጓደኞቹ እኩል እንዲማር ስላደረገው ተደስቷል። በገረብ ፀዶ ትምህርት ቤት እየተማሩ ካገኘናቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሀብታሙ ተመስገን ሁሉም የትምህርት ቁሳቁሶች ተሟልቶልኛል ሲል ተናግሯል። “በተደረገልኝ ድጋፍ ተጠቅሜ ትምህርቴን ጠንክሬ እማራለሁ” ብሏል። በመቀሌ ከተማ ሀወልት ክፍለ ከተማ የሚኖሩ ተፈናቃይ የዕብዮ አለነ  ልጆቻችን እንዲማሩና ጊዜያዊ ድጋፍ እንድናገኝ የተደረገው ጥረት መልካም ነው” ብለዋል። ‘‘በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችለን ድጋፍ ግን አሁንም ገና ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም