በአካባቢያችን በተገነባው 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የረዥም ጊዜ ጥያቄያችን ተመልሷል-.. የኢሉ ገላን ወረዳ ነዋሪዎች

124
አምቦ መስከረም 18/2011 በአካባቢያችን በተገነባ ትምህርት ቤት በዚህ አመት ልጆቻችንን የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ለማስተማር በተፈጠረልን እድል የረዥም ጊዜ ጥያቄያችን ተመልሷል ሲሉ በምእራብ ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የኢሉ ገላን ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ መንግስት በመደበው 11 ሚሊዮን ብር ወጭ ግንባታው የተጠናቀቀ የቂልጡ ኢላላ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን የወረዳው ትምህርት ቤቶች ፅህፈት ቤት አስታውቋል ። በወረዳው የአሌ ወረ ኢሉ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ተሠማ ከበደ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የተገነባው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ልጆቻቸው በአቅራቢያቸው ትምህርቱን እንዲጀምሩ ዕድል በመፍጠሩ የህዝቡን ጥያቄ የመለሰ ነው ። "ከዚህ ቀደም ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ የአካባቢው ልጆች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል እርቀው ይሄዱ ነበር " ያሉት አቶ ተሠማ ትምህርት ቤቱ በአካባቢው መገንባቱ ተማሪዎችን  ከእንግልት፣ ወላጆችን ደግሞ ከወጭ የሚታደግ መሆኑን ተናግረዋል ። አቶ ኢጃራ ፈይሣ በበኩላቸው ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ ሁለት ልጆቻቸውን በአቅም ማነስ ምክንያት ወደ ሌላ አካባቢ ልከው ለማስተማር ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን አቋርጠው መቆየታቸውን አስታውሰዋል ። ልጆቻቸው ዘንድሮ በአካባቢው በተገነባው ትምህርት ቤት በመግባት ትምህርታቸውን ለመከታተል እድሉ ስለተፈጠረላቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልፀዋል ። "መንግስት ጥያቄያችንን አዳምጦ ምላሽ ስለሰጠን እናመሰግናለን" ብለዋል። "የአካባቢው ነዋሪዎች የተገነባልንን ትምህርት ቤት ከመጠበቅ ጀምሮ የሚጠበቅብንን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ያሉት ደግሞ አቶ አብርሃም በዳዳ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡ የኢሉ ገላን ወረዳ ትምህርት ቤቶች  ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተፈሪ ድሪባ በበኩላቸው መንግስት የህዝቡን ጥያቄ በመቀበል በ11 ሚሊዮንብ ወጭ ትምህርት ቤቱን መገንባቱን ተናግረዋል። የትምህርት ቤቱ ግንባታ ሁለት አመት ጊዜ መፍጀቱን የገለፁት ኃላፊው፣ ትምህርት ቤቱ በአንድ ጊዜ 2ሺህ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመስተማር አቅም እንዳለው አስረድተዋል ። በተያዘው የትምህርት ዘመን ከወረዳውና በዙሪያው ካሉ አንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል ትምህርት ቤቶች 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁ 1ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን ኃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም