በሴቶችና ሕጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የችግር አሳሳቢነት የሚመጥን የጋራ ስራ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

163

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 1/2015 በሴቶችና ሕጻናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት የችግር አሳሳቢነት የሚመጥን የጋራ ስራ ማከናወንና ፈጣን ምላሽ መስጠት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

"ሴቶችን አከብራለሁ፤ ጥቃታቸውን እከላከላለሁ" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ለ15 ቀናት ሲካሔድ የቆየው ሴቶችን ከጥቃት የመከላከል ንቅናቄ ዛሬ ተጠናቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አራጋው፤ በቢሮው በኩል የተለያዩ የመከላከል ስልቶች ተግባራዊ እየሆኑ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በዘጠኝ ክፍለ ከተሞች ከ1 ሺህ 130 በላይ አባላት ያሉት የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል።

ለቢሮው በየቀኑ በአማካይ ስድስት የሚደርሱ የጾታዊ ጥቃት ኬዞች እንደሚደርሱት ገልጸው ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር በቀጣይ ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን የመደፈር፣ የመደብደብና ተያያዥ ወንጀሎች ለመከላከል ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ነው ወይዘሮ ሜሮን ያመለከቱት።

በሴቶችና ሕፃናት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት በጋራ መከላከል ይገባል ነው ያሉት።

የፀጥታ ተቋማትና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት አጠቃላይ ማህበረሰቡ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የሴቶችን ጥቃት የመከላከል (የነጭ ሪቫን) ቀን በዓለም ለ31ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ17ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም