መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ለሚያከናውናቸው ስራዎች የአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

310

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ህዳር 30/2015  የኢትዮጵያ መንግስት በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም ለሚያከናውናቸው ስራዎች የአውሮፓ ህብረት የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንዲያደርግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በሰላም ስምምነቱ ትግበራ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት በተለያዩ ዘርፎች ያላቸውን ጠንካራ ትብብር አጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በመንግስትና ህወሀት መካከል የተደረገው ስምምነት ተከትሎም ጦርነቱን ማስቆም መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ ለፖለቲካዊ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሄ በማምጣት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማጽናት ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

ስምምነቱን በመተግበር ረገድ ኢትዮጵያ በወሳኝ ምእራፍ ውስጥ እንደምትገኝም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

ስምምነቱን ተግባራዊ የማድረጉ ስራ የቴክኖሎጂና ሎጂስቲክስ ግብዓቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የአውሮፓ ህብረት የሚጠበቅበትን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችንና ጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት የአውሮፓ ህብረት እንዲደግፍ ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን እያደረገ ያለውን ድጋፍ ኢትዮጵያ እንደምታደንቅ በመግለጽ መንግስት በአካባቢው ዘላቂ ስላም እንዲሰፍን የሚጠበቅበትን ሚና እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡