የእንቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የመላ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ያስፈልጋል- ቋሚ ኮሚቴው

168

ባህር ዳር(ኢዜአ) ህዳር 30 ቀን 2015 የእንቦጭ አረምን ከጣና ሃይቅ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የመላ ኢትዮጵያዊያን ያልተቋረጠ ድጋፍና እገዛ እንደሚያስፈልግ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሃ ፣መስኖ፣ ቆላማ አካባቢዎችና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።

ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በአስተዳደሩ በተለምዶ "ይባራ" ተብሎ በሚጠራ የጣና ሃይቅ ዳርቻ ዛሬ  የእንቦጭ አረም የማጽዳት ስራ አከናውነዋል።

በዚህ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው አባል  አቶ አጉ ደባን ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቋሚ ኮሚቴው  በተለይ በውሃ ሃብት ላይ የሚከናወኑ ስራዎችን ይከታተላል።

ዘንድሮ ትኩረት ተሰጥቶ ከሚሰራባቸው  መካከል ጣና ሃይቅ ላይ ያለውን የእንቦጭ አረም በማስወገድ የውሃ አካሉ ተገቢው ደህንነት እንዲጠበቅ ማስቻል እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

ጣና ሃይቅ የመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ሀብት በመሆኑ አረሙን ከሃይቁ ላይ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት የመላ ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍና ትብብር እንደሚያሻ ገልጸዋል።

ጣና ሃይቅና የዓባይ ወንዝ የተሳሰሩ በመሆናቸው የሀገር ሃብት ብቻ ሳይሆን ከዛ ያለፈ ትርጉም እንዳለው  ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው  የእንቦጭ አረም ከሃይቁ ላይ እንዲወገድ ለማስቻል የሚረዱ ዝርዝር የስራ ዕቅድ  ነድፎ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው፤  ይህ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት በወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የእንቦጭ አረም ለማስወገድ ተገቢ የሆነ ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የጣናና ሌሎች ውሃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ ናቸው።

ሆኖም  ከዛ በፊት በነበሩ የዘመቻ ስራዎች   አረሙ እንዳይስፋፋ ማድረጉን አውስተዋል።

አረሙ ባለፉት ዓመታት እስከ 20 ሺህ ሄክታር ድረስ የሃይቁን ክፍል ሸፍኖት እንደነበር አስታውሰው፤  ህዝቡን በማነቃነቅ በተከናወነው ተከታታይ ስራ  ሽፋኑንም ከሁለት ሽህ ሄክታር በማይበልጥ ሁኔታ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።

በየደረጃው ያለው አመራር ህዝቡን በማስተባበር  ከዘመቻ ስራ ወጥቶ  አረሙን ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት መረባረብ እንዳለበት አሳስበዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳትና ውበት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አወቀ ፈንታ በበኩላቸው፤ ጣናንና ባህር ዳር ከተማን ነጣጥሎ ማሰብ እንደማይቻል ተናግረዋል።

አረሙ እስኪጠፋ ድረስ ህዝቡን በማስተባበር የማጽዳት ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ዛሬም ከሁለት ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር የማጽዳት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በዛሬው ስራ ከተሳተፉት መካከል ወይዘሮ መዲና ተስፋ በሰጡት አስተያየት፤ ጣና ሃይቅን በእንቦጭ አረም ከተደቀነበት አደጋ መከላከል ለተወሰኑ አካላት ብቻ የሚተው እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማጥፋት ካለፉት 11 ዓመታት ጀምሮ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የዘመቻ ስራ ሲከናወን መቆየቱ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም