በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የበረራ ደህንነት ዘርፍ ተግባራት ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ምሳሌ መሆናቸው ተገለጸ

135

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 30 ቀን 2015 በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የበረራ ደህንነት (የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ) ዘርፍ የሚያከናውናቸው የበረራ ደህንነት አገልግሎት ስራዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተምሳሌት መሆን እንደሚችል ተገለጸ።

የአሜሪካ ትራንስፖርት ደህንነት መስሪያ ቤት (TSA) የኦዲት የልዑካን ቡድን ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ያከናወነውን አጠቃላይ የበረራ ደህንነት (የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ) ኦዲት ስራ አጠናቋል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በቆይታው የበረራ ደህንነት (የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ) ዘርፍ የሚያከናውናቸውን የመንገደኞች፣ የሻንጣ፣ የካርጎ ጭነት፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ፍተሻ፣ ደህንነት አጠባበቅና ቁጥጥርና የእጀባ ስራ ተመልክቷል።

በዚህም አጠቃላይ አሰራርና የቅድመ መከላከያ ዘዴ አተገባበር ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑና ከአለም ዓቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የተወሰዱና የበረራ ኢንዱስትሪው የሚገለገልባቸውን የተለያዩ ሰነዶች ከአተገባበር አንፃር በማመሳከር በጥልቀት የመመርመር ተግባር አከናውኗል፡፡

ቡድኑ በማጠቃለያው በሰጠው መግለጫ በበረራ ደህንነት ዘርፍ እየተሰጠ የሚገኘው አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለውና በአስተማማኝ የበረራ ደኅንነት ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን አረጋግጧል።

እየተከናወነ የሚገኘው ስራ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጭምር ተምሳሌት መሆኑንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ለደረሰበት ከፍታ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የበረራ ደህንነት (የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ) ዘርፉ ጎልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስታውቋል፡፡

በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የአቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የበረራ ደህንነት ዘርፍ እና በኤርፖርቱ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሌት ተቀን በጋራ በመስራታቸው ኦዲቱን ያለምንም ግኝት በስኬት ማጠናቀቅ ተችሏል።

የተገኘው ውጤት ለሀገራችን የበረራ ኢንዱስትሪ ዘርፍና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም