የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የሶማሊያ ፖሊስ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

155

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 30/2015 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስና የሶማሊያ ፖሊስ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱ ድንበር ዘለል በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ሲሆን በተለይ ሽብርተኝነትንና ህገ-ወጥ የሰዎችንና ጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በጋራ መስራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ስምምነቱ የሶማሊያ ወጣት ፖሊስ አመራሮች በኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ ገብተው ስልጠና እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን በቅርቡ ከ40 በላይ የሚሆኑ የሶማሊያ ፖሊስ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ስልጠና እንደሚወስዱ ተገልጿል።

ስምምነቱን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከሶማሊያ አቻቸው ሜጀር ጀነራል አብዲ ሀሰን መሀመድ ጋር ነው የተፈራረሙት።

ላለፋት 6 ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 24ኛው የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም