በደቡብ ክልል በእንስሳትና አሳ ሃብት ልማት 25 ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን እና ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

163

ህዳር (ኢዜአ) 30/2015 በደቡብ ክልል የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ከ25 ሺህ በላይ አነስተኛ ገቢ ያላቸው አርሶ አደሮችን፣ ሴቶችን እና ስራ አጥ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ተጠቃሚዎች ፕሮጀክቱ ባደረገላቸው ድጋፍ ከነበሩበት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ተላቀው ቤተሰቦቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ከማስተዳደር ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ከዓለም ባንክ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን በወተት፣ በዶሮ እርባታ፣ በቀይ ስጋ እና በዓሳ ሃብት ልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል።

ፕሮጀክቱም ከ1 ሚሊየን 27 ሺህ በላይ የጋራ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖችን በማደራጀት እንዲሁም ከ42 በላይ የአርሶ አደር ማህበራትን በማደራጀት በአሁኑ ጊዜ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ይገኛል።

ኢዜአ በደቡብ ክልል የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት ትግበራን በአካባቢው ተገኝቶ ቃኝቷል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ተስፋዬ  እንደገለጹት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ ሴቶች እና ስራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት በወተት፣ በስጋ፣ በአሳ እና በዶሮ እርባታ ልማት እንዲሰማሩ መደረጉን አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱም የእንስሳት ሃብት የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማሻሻል በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በክልሉም ከ1 ሺህ 900 በላይ የጋራ ፍላጎት ያላቸውን አርሶ አደሮች፣ ሴቶች እና ስራ አጥ ወጣቶችን በቡድን በማደራጀት ከ25 ሺህ በላይ ዜጎችን ቀጥተኛ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

የጋራ ፍላጎት ያላቸውን ቡድኖች በማደራጀት እስከ 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚደርስ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማድረግ ወደ ህብረት ስራ ማህበራት እና ዩኒየን እንዲሸጋገሩ እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ እያካሄደ ባለው የወተት፣ የቀይ ስጋ፣ የዓሳ እና የዶሮ እርባታ ልማት ዘርፍ ላይ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከፍ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

የደንባ ጎፋ ወረዳ እና የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የእንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አለሙ በርዛ እና አቶ አብዮት አንጂሎ እንደሚሉትም ፕሮጀክቱ የበርካታ ዜጎችን ኑሮ ማሻሻል ችሏል።

የአካባቢውን ስነ-ምህዳር በጠበቀ መልኩ እየተካሄደ በሚገኝ ልማትም በአንድ ዙር ከ20 ሺህ ብር በላይ የሚደርስ ትርፍ እያገኙ ልጆቻቸውን በጥሩ ሁኔታ እያስተማሩ ለሌሎች አርሶ አደሮችም የዕውቀት ሽግግር እያደረጉ እንደሚገኝ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ከነበሩበት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በመላቀቅ ቤተሰቦቻቸውን በተሻለ ሁኔታ ከማስተዳደር አልፈው ለአካባቢው ማህበረሰብ ምሳሌ ለመሆን መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ እ.አ.አ. ከ2018 ጀምሮ በ58 ወረዳዎች በ1ሺህ 755 ቀበሌዎች የአርሶ አደሩን የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም