ብልጽግና ፓርቲ 1ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ጀመረ

136

ሕዳር 30/2015 (ኢዜአ) ብልጽግና ፓርቲ አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን በሀዋሳ ከተማ በማካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የስራ አስፈፃሚ እና የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም በፓርቲው መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አመራሮች መታደማቸው ተገልጿል።

ጉባኤውን በአስቸኳይ ማድረግ ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት መጋቢት ላይ በተካሄደው የፓርቲው የመጀመሪያው ጉባኤ በምርጫ ቦርድ ያልተሟሉ አንድ አንድ ነጥቦች መታረም እንደሚገባቸው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ነው፡፡

ፓርቲው በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ እንደገለጸው የምርጫ ቦርድን የማስተካከያ ትእዛዝ በመቀበል ጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት በመጋበዝ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል፡፡

ብልፅግና ይህን አስቸኳይ ጉባኤ ማካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት መሆኑን የገለጸው ፓርቲው እንደ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለመገንባት ያለው ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብሏል፡፡

በተጨማሪም በፓርቲው መሪነት የተጀመረው የተቋም ግንባታ ሀሳብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ለሌሎች ፓርቲዎች ጭምር ሁነኛ ምሳሌ መሆን የሚችል ተግባር መፈፀም የሚገባ መሆኑ ታምኖበት እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም